Sunday, September 22, 2024
spot_img

በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ በሁለት ወራት ብቻ ከ146 ሺሕ በላይ እንስሳት ሞተዋል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 11 2014 ― በሶማሌ ክልል በሚገኙ 78 ወረዳዎች ላይ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በሁለት ወራት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከ146 ሺሕ በላይ ከብት፣ ግመልና ፍየሎች መሞታቸውን የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ አስታውቋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙት 11 ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና በሲቲ ዞን ውስጥ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ዕርዳታ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር ወደ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ከፍ እንዳለም ተገልጿል፡፡

የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ በሽር ዓረብ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደነገሩት፣ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙት 11 ዞኖች ውስጥ ዘጠኙ ዝናብ ያገኙ የነበሩት ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ በመኸርና በበልግ ወራት ነው፡፡

ይሁንና በ2013 ከሚያዝያ እስከ ሰኔ የቆየው የበልግ ወቅት የዘነበው ዝናብ ዝቅተኛ በመሆኑና አሁን እየተጠናቀቀ ባለው የመኸር ወቅት ሙሉ በሙሉ ባለመዝነቡ በክልሉ ውስጥ የተከሰተው ድርቅ ስድስት ወራት ሆኖታል፡፡ እነዚህ ዞኖች የተያዘው ወር ድረስ ማግኘት የነበረባቸውን ዝናብ ባለማግኘታቸውና ደረቅ የሆነው የበጋ ወቅት እየገባ በመሆኑ ድርቁ ይቀጥላል የሚል ሥጋት እንዳለ ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ ያለው ድርቅ በተለይ በዳዋ፣ አፋሌር፣ ሸበሌና ኮራይ ዞኖች ተፅዕኖው እንደከፋ የተገለጸ ሲሆን፣ ድርቁን መቋቋም ያቃታቸውና አቅም ያላቸው ነዋሪዎች እንስሳቶቻቸውን በመኪና እየጫኑ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ወደ ጅግጅጋ አቅራቢያ መምጣታቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም እንስሳቶቻቸው በድርቁ እጅጉን በመጎዳታቸው በጉዞ ላይ እያሉና ከመኪና ሲወርዱ ሕይወታቸው እያለፈ እንደሚገኝ አቶ በሽር ተናግረዋል፡፡

ጥቂት የማይባሉ ዞኖች ላይ እየሞቱ ያሉት እንስሳት ቁጥር ሪፖርት ባለመደረጉ፣ ባለፉት ሦስት ወራት ገደማ ውስጥ የሞቱ እንስሳት ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የብሔራዊ ሜትሮሎጂ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሚያዝያ ወር 2014 አንስቶ የሚገባው ቀጣዩ በልግ ላይ የሚኖረው የዝናብ መጠን ከመደበኛው ዝቅተኛ እንደሚሆን ትንበያውን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዚህም ድርቁ ከአንድ ዓመት በላይ ሊዘልቅ ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን አቶ በሽር ዓረብ ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img