Sunday, November 24, 2024
spot_img

መንግሥት እነ ጀዋር ሙሐመድን ጨምሮ ፖለቲከኞችን ከእስር ሊፈታ እንደሆነ ታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 11 2014 ― መንግሥት በእስር ላይ ያሉትን አቶ ጀዋር ሙሐመድና ሌሎች ፖለቲከኞችን ከእስር ሊፈታ እንደሆነ ታውቋል፡፡

አምባ ዲጂታል ከቅርብ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሠረት በእስር ላይ የሚገኙ በርካታ ፖለቲከኞችን ለመፍታት በመንግሥት በኩል ውሳኔ እንደተደረሰበትና፣ ለተግባራዊነቱም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተሰምቷል።

በቀዳሚነት ከእስር ቤት እንደሚፈቱ ከተሰሙት መካከል የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተነሳ ግርግር ለእስር የተዳረጉት የኦፌኮ ፓርቲ አመራሮቹ አቶ ጀዋር ሙሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የኦነግና የኦፌኮ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም አክቲቪስቶች እንደሚገኙበት ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት ከመንግሥት የተላኩ የሀገር ሽማግሌዎች ወደ ቃሊቲ በማቅናት እስረኞቹን ለመፍታት ውሳኔ ላይ እንደተደረሰና ዝግጅትም እየተደረገ እንደሚገኝ ለእስረኞቹ እንደነገሯቸው የአምባ ዲጂታል ታማኝ ምንጮች ጨምረው ጠቁመዋል።

በመንግሥት በኩል የሚወሰደው ከእስር የመፍታት እርምጃ የባልደራስ ፓርቲ አመራር የሆኑትን አቶ እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮልን ሳይጨምር እንደማይቀርም ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት «የሀገራችንን ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላም እንዲሁም ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት» ያለመ ነው የተባለለት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ኪሚሽኑም በገለልተኛ ግለሰቦች እንዲመራ አቅጣጫ መቀመጡ ተሰምቷል።

በመንግሥት በኩል ይወሰዳል ተብሎ የሚጠበቀው ፖለቲከኞቹን የመፍታት እርምጃ በቅርቡ ይጀመራል ለሚባለው ይህ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የዝግጅት አካል እንደሆነ ተነግሯል። ሀገራዊ ምክክርና ቀጣይ ሂደቱን በተመለከተ የብልጽግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የየአካባቢው ባለሥልጣናት ውይይት ማካሄድ የጀመሩ ሲሆን፣ ለዚሁ ሀገራዊ ውይይት አቅጣጫ የሚሰጥ አዋጅና ኮሚሽኑን የሚመሩ ግሰለቦች ስም ዝርዝር በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

አሁን ከእስር ሊፈቱ መሆኑ የተነገረላቸው አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በርካቶች በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኔ 23፣ 2012 ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img