Thursday, November 28, 2024
spot_img

ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ ኢትዮጵያን የአደጋ ሥጋት አንዣቦባቸዋል ካላቸው ቀዳሚ አገራት መካከል አስቀመጠ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ታኅሣሥ 10፣ 2014 – በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ ለሆኑ የሰብዓዊ ቀውሶች ምላሽ በመስጠት ሰዎችን ማዳን ተግባሩ እንደሆነ የሚገልጸው ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያን በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት የአደጋ ሥጋት አንዣቦባቸዋል ካላቸው 10 የዓለም አገራት መካከል በ2ኛ ደረጃ አስቀምጧታል፡፡

ኮሚቴው ኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት አንዣቦባታል ያለው ከቀጠለው ግጭት እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ ይኸው የአየር ንብረት ለውጥ እና በትግራይ ተጀምሮ ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ግጭት ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከአደጋ ሥጋት ጋር በተገናኘ ወደ ፊት እንደገፋት አሳውቋል፡፡

ድርጅቱ የአሜሪካ መንግስትን ጠቅሶ ከአገሪቱ አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ብቻ ወደ 900 ሺሕ ሰዎች ድርቅ እንደተጋረጠባቸው ገልጧል፡፡ በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥ ሚሊዮኖችን ለዚሁ ችግር እንደሚዳርጋቸውም ግምቱን አስቀምጧል፡፡

ከነዚህ ሁለት የአደጋ ሥጋቶች ናቸው ብሎ ከጠቀሳቸው ምክንያቶች ውጪ በኢትዮጵያ የኮቪድ ወረርሽኝ ክትባት ሥርጭት አነስተኛ መሆኑን የጠቀሰው ድርጅቱ፣ ይህ መሆኑ በቀጣይ ጊዜያት የኮቪድ ተጋላጭነትን እንደሚጨምር ነው ያመለከተው፡፡  

ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ በቀጣዩ ዓመት በአደጋ ሥጋት ከዓለም አገራት በቀዳሚነት ያስቀመጠው ባለፉት ዓመታት ሰላም የራቃት አፍጋኒስታንን ነው፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ መረጋጋት የራቃቸው የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት ሱዳን እና ሶማሊያ፣ ሌላኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ አገር ደቡብ ሱዳን፣ ማይናማር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ፣ የመን እና ሶሪያን በዝርዝሩ አካቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img