አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 8፣ 2014 ― የዛሬ ሳምንት ዐርብ ታኅሣሥ 1፣ 2014 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ታምራት ነገራ ትላንት ታኅሣሥ 7፣ 2014 በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ገላን ፍርድ ቤት መቅረቡ ተነግሯል።
እንደ ዋዜማ ራድዮ ዘገባ ከሆነ ታምራት ፍርድ ቤት የቀረበው ያለ ጠበቃ ነው።
ታምራት ነገራን በተመለከተ ቀድሞ አዲስ አበባ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዷል ብንባልም ያለበትን ማወቅ አልቻልንም ያሉት ቤተሰቦቹ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር አይዘነጋም።
የታምራት ነገራን ደብዛ መጥፋት ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተራራ ኔትወርክ መስራቹ ታምራት እንዲሁም ላለፉት 27 ቀናት ደብዛው ጠፍቷል የተባለው የአሐዱ ራዲዮ አርታኢ ክብሮም ወርቁ ያሉበት ይፋ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።
ታምራት ነገራ ለምን እንደታሰረ እስካሁን ባይነገርም፣ በትላናትናው እለት መግለጫ ያወጣው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ በኢትዮጵያ ከጥቅምት 23፣ 2014 ጀምሮ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ ታምራትን ጨምሮ 14 ጋዜጠኞች መታሠራቸውን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በተመሳሳይ ባለፉት አስር ቀናት ከታሰሩ ሚዲያ ላይ ከሚሠሩ መካከል እያስጴድ ተስፋዬ ከኡቡንቱ ቲቪ እና መዐዛ መሐመድ ሮሃ ከተሰኘ የበይነ መረብ ሚዲያ ይጠቀሳሉ፡፡