Saturday, November 23, 2024
spot_img

የመብት ተቋማቱ በምዕራብ ትግራይ በትግራይ ተወላጆች ላይ አዲስ የመብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 8፣ 2014 ― ዓለም አቀፍ የመብት ተቋማት የሆኑት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሒዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ በትግራይ ተወላጆች ላይ በቅርብ ጊዜያት አዲስ የመብት ጥሰት እየተፈጸመ ስለመሆኑ የሚገልጽ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡

ተቋማቱ በጋራ ባወጡት ሪፖርት በምዕራብ ትግራይ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የተለያዩ ከባድ የመብት ጥሰቶችን እየተፈጸመ የሚገኘው በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት በዚህ አካባቢ በጸጥታ ኃይሎቹ በወሰዱት እርምጃ የጅምላ ግድያዎች፣ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች እና መፈናቀል መመዝገቡን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ላወጡት ሪፖርት በጥቅምት እና ኅዳር ወራት በአጠቃላይ ሰዎች ሰዎችን በስልክ አናግረናል ብለዋል፡፡

ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ የአማራ ክልል ፖሊስና ሚሊሻ እንዲሁም ፋኖ የተባለው መደበኛ አደረጃጀት የሌለው ቡድን በአደባይ፣ በሁመራ እና በራውያን ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን በመክበብ ቤተሰቦችን ለያይተው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑትን ወንዶችንና ሴቶችን በቁጥጥር ስር አውለዋል መባሉም በሪፖርቱ ሠፍሯል፡፡

ሪፖርቱ በትግራይ ተወላጆች ላይ ይደርሳል ላለው በደል በማሳያነት ከጠቀሳቸው መካከል ጥቅምት 24፣ 2014 ማለዳ በአደባይ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ለጸሎት ወደ አቡነ ተክላይ ቤተክርስትያን እያቀኑ ባሉበት የአካባቢው የጸጥታ አካላት ሴቶቹን እንዲሄዱ በማድረግ፣ ወንዶቹን ስብሰባ አለ በማለት እንዲሰበሰቡ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ስብሰባ በመሸሽ ለማምለጥ የሞከሩ ላይ እንደተተኮሰባቸው እንዲሁም ድብደባ እንደተፈጸመባቸውም ሠፍሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፋኖ አባላት የቤት ለቤት አሰሳ እንዳደረጉም ተጠቅሷል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቀውስ ጊዜ ምላሽ ኃላፊ ጆአኒ ማሪነር በአካባቢው በአማራ ክልል ኃይሎች በትግራይ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ አዲስ የተቀሰቀሰው ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ ተጨማሪ ጭፍጨፋዎችን ለማስቆም አስቸኳይ ዓለም አቀፍ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የመብት ተቋማቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጡት ሪፖርት የመንግስት ባለሥልጣናት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲያቆሙ፣ ከሕግ ውጪ የተያዙ ሰዎች እንዲለቀቁ እና የእርዳታ ድርጅቶች ወደ አካባቢው እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img