አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 7፣ 2014 ― የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በመጪው ዐርብ እንዲካሄድ የጠራውን ልዩ ስብሰባ እንደማይቀበልና በዚህ ስብሰባ የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ዐ ስታውቋል፡፡
የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ የዐርብ ስብሰባውን የጠራው የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከምክር ቤቱ አባላት እና ታዛቢዎች የቀረበለትን አስቸኳይ ጥያቄ ከተቀበለ በኋላ መሆኑ መነገሩ አይዘነጋም፡፡
ሥነ ሥርዓቱን አስመልክቶ የምክር ቤቱ ቢሮ ትላንት ረቡዕ ታኅሣሥ 6፣ 2014 በተወያየበት ወቅት በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ አምባሳደር ማሕሌት ኃይሉ ተገኝተው የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም አስረድተዋል።
አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ላይ የተጠራው ልዩ ስብሰባ የምክር ቤቱን የአሠራር ደንብ ያልተከተለና የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ ለፖለቲካዊ ፍላጎቶች መጠቀሚያ የሚያደርግ እንዲሁም፣ ምክር ቤቱ አባል አገሮች ላይ መድሎ እንዲፈጽምና በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያዩ አሠራሮችን እንዲከተል በማድረግ ተቋማዊ ኃላፊነቱን የሚያረክስ እንደሆነ መናገራቸውንም የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።
አባል አገሮቹ ይህንን ያልተገባ አሠራርና አንዳንድ አገሮች ሰብዓዊ መብትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በምክር ቤቱ በኩል ለማስፈጸም የሚያደርጉትን ጥረት በማውገዝ የምክር ቤቱ ተቋማዊ መርሆዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በዋናነት ስብሰባውን የጠራው የአውሮፓ ህብረት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶችን የሚመረምር ዓለም አቀፍ የባለሞያዎች ቡድን በኢትዮጵያ እንዲሰማራ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በአውሮፓ ኅብረት አማካይነት ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር በጥምረት ያደረጉት ምርመራ ውጤትን መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲሰማራ የሚጠይቅ ነው።
ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድኑ የአንድ ዓመት ቆይታ እንዲኖረው የሚጠይቀው ይኸው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ፣ የሚላከው ቡድን ከሚያደርገው ምርመራ በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ የሚደረግበትን፣ ዕርቅና ተጠያቂነት የሚሰፍንበትን እንዲሁም፣ ሰብዓዊ ጥስት የደረሰባቸው ማገገም እንዲችሉ ምክረ ሐሳብና የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት እንዲኖረውም ይጠይቃል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ስብሰባውን የሚያካሄደው በመጪው ዐርብ ታህሳስ 8፤ 2014 ከቀኑ 12 ሰዓት ጀምሮ መሆኑን በትዊተር ገጹ አሳውቋል፡፡