Saturday, September 21, 2024
spot_img

በቀጣይ ወር ይፋ እንደሚደረግ የሚጠበቀው ሁለተኛው የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ሊሠረዝ ወይም ሊራዘም ይችላል ተባለ

 

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 7፣ 2014 ― በቀጣዩ ጥር ወር ይፋ እንደሚደረግ የሚጠበቀው ሁለተኛው የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ሊሰረዝ ወይም ሊራዘም ይችላል የተባለው ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ጋር በተገናኘ በርካታ ኩባንያዎች ሥጋታቸውን በማቅረባቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡  

በጉዳዩ ላይ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በርካታ የምዕራባውያን ሚዲያዎችና ተቋማት፣ የፌደራል መንግሥት በሕወሓት ታጣቂዎች እየተሸነፈ የሚመስል መረጃ በመንዛታቸው፣ በኢንቨስተሮች ላይ ከፍተኛ ጫና መፈጠሩን መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ውሳኔ ላይ የሚደርሱት አገራዊና ወቅታዊ ሁኔታውን ካጠኑ በኋላ ለቦርድ አባላቶቻቸው ወይም ለፋይናንስ ምንጮቻቸውና አጋሮቻቸው አቅርበው፣ ‹‹አሁን ጨረታ አስገቡ›› የሚል ትዕዛዝ ሲደርሳቸው እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምዕራባውያን ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ በሚያሠራጩት የተዛባ መረጃ ምክንያት በጨረታው ሊሳተፉ ፍላጎት ያላቸው በርካታ ኩባንያዎች፣ የጨረታው ጊዜ እንዲገፋ ወይም ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም የተለያዩ ጥያቄዎች እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከውጭ ኩባንያዎች በተጨማሪ ከአገር ውስጥም ቁጥራቸው ከፍ ያለ ባለሞያዎች በዚህ ወቅት ጨረታ ማውጣቱ ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ሥጋታቸውን በመግለጽ፣ ጥንቃቄ እንዲደረግበት አስተያየታቸውን እየሰጡ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

ከኩባንያዎችና ከባለሞያዎች እየቀረበ ያለውን የሥጋት አስተያየት በመገንዘብ፣ ኢንቨስተሮች ያቀረቡት ሐሳብ ላለመወዳደር ከመፈለግ እንዳልሆነ በመረዳትና በተለይም በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች የተነሳ፣ የኢንቨስትመንት ዕቅዳቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር፣ የማስተካከያ ዕርምጃ ለመውሰድ መታሰቡን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የቀረበውን ሐሳብ ግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹ጨረታው ይሰረዝ፣ ወይም ለሌላ ጊዜ ይራዘም›› የሚለውን ውሳኔ መንግሥት በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ የወጣው መስከረም 18፣ 2014 እንደነበር አይዘነጋም፡፡

መንግሥት ከዚህ ቀደም የቴሌኮሙዩኔኬሽን ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ በወሰነው መሠረት፣ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሁለት ኩባንያዎች ለ15 ዓመታት አገልግሎቱን ማቅረብ የሚችሉበት ፈቃድ ለመስጠት በ2013 ባወጣው የመጀመሪያ ጨረታ ‹‹ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ›› የተባለው የኩባንያዎች ጥምረት አንደኛ አሸናፊ መሆኑም ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img