Saturday, November 23, 2024
spot_img

መንግሥት ፖለቲካዊ አላማ አለው ያለውን የተመድ ስብሰባ፤ የሰብዐዊ መብት ም/ቤት አባላቱ ውድቅ እንዲያደረጉት ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 5፣ 2014 ― መንግሥት ፖለቲካዊ አላማ አለው ያለውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የተመድ) የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት የፊታችን ዐርብ የጠራውን ልዩ የተባለ ስብሰባ የምክር ቤት አባላት ውድቅ እንዲያደርጉት ጠይቋል፡፡

የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ የሚያደርገውን ስብሰባ የጠራው የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከምክር ቤቱ አባላት እና ታዛቢዎች የቀረበለትን አስቸኳይ ጥያቄ ከተቀበለ በኋላ ነው፡፡

ነገር ግን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ በጄኔቭ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ላይ እየታየ ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያን ግራ ያጋባና ያሳዘነ መሆኑን ገልጧል፡፡

መግለጫው አያይዞም የሰብዓዊ መብቶች የጋራ መርማሪ ቡድን ባለፈው ወር በኢትዮጵያ ያደረገውን ምርመራ ውጤቱን ይፋ ባደረገው የሰብአዊ መብት ምርመራ ሪፖርት የተቀመጡ ምክረ ኃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል በመግባት፣ ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ባለበት ሁኔታ አንዳንድ የጉባኤው አባላት መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት በቸልታ መመልከት እንደመረጡ አስታውቋል።

የፖለቲካ ጫና ለማሳደር በሚደረጉ ኢ-ፍትሃዊ እና ውጤታማ ያልሆኑ ሙከራዎች ሰለባ ስትሆን ለኢትዮጵያ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም ያለው መግለጫው፣ በ47ኛው የምክር ቤቱ ጉባዔ የኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እንዲያጠናቅቅ ተደጋጋሚ ትብብርና እውቅና ብትሰጥም፣ የጉባኤው አባል ሃገራት የሚመለከተውን አገር ያላሳተፈ የውሳኔ ሐሳብ ለማፅደቅ ጥረት ላይ እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አባላት እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በአለም አቀፍ ህግጋት መሰረት የሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ግዴታዎቹን ለመወጣት ቁርጠኛ እንደሆነም መግለጫው አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ስብሰባውን የሚያካሄደው በመጪው ዐርብ ታህሳስ 8፤ 2014 ከቀኑ 12 ሰዓት ጀምሮ መሆኑን በትዊተር ገጹ አሳውቋል፡፡

47 አባላትን የያዘው ዋና ጽሕፈት ቤቱን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ ያደረገው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በጠቅላላ ጉባኤው 13 መቀመጫዎችን ለአፍሪካ አህጉር ደልድሏል፡፡

አፍሪካን ወክለው የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ አገራት መካከል የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የሆኑት ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ አገራት የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ለመገምገም አስቸኳይ ስብሰባ እንዲካሔድ ጥሪ ካቀረቡት መካከል የሉበትም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img