አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 4፣ 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የተመድ) የሰብአዊ መብቶች ም/ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ልዩ ስብሰባ ሊያደርግ መሆኑ ተነግሯል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ ልዩ ስብሰባውን የሚያደርገው በዚህ ሳምንት ሲሆን፣ ስብሰባውን የሚያደርገው ከአውሮፓ ህብረት የቀረበለትን አስቸኳይ ጥያቄ ከተቀበለ በኋላ ነው።
የአውሮፓ ህብረት ለምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በላከው ደብዳቤ የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛው የመብት አካል በኢትዮጵያ ለ13 ወራት በተሻገረው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ስለቀጠፈው እና አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ያስከተለበትን ሁኔታ በፍጥነት እንዲፈታ አሳስቧል።
የአውሮፓ ህብረት ጥሪው የመጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመብት ኃላፊ ሚሼል ባቸሌት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ባወጡት የጋራ ሪፖርት በግጭቱ ውስጥ በሁሉም ወገኖች ከባድ በደል መፈጸሙን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳለ ባለፈው ወር ካስታወቁ በኋላ መሆኑን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመብት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በወቅቱ ባወጡት ሪፖርት ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ጥሰቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመው ነበር።