Sunday, September 22, 2024
spot_img

በሶማሌ ክልል እስር ላይ የነበሩት የነበድ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በ20 ሺሕ ብር ዋስትና ተለቀቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 4፣ 2014 ― ባለፈው ወር ኅዳር መጀመሪያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ‹ነበድ› የተሰኘ ቴሌቪዥን ባልደረባ የሆኑ አራት ጋዜጠኞች መለቀቃቸው ተሰምቷል፡፡

ታስረው የነበሩት ኢብራሂም ሑሴን፣ ሰልማን ሙኽታር፣ መሐመድ ቃሲም እና ሒርሲ መሐመድ እያንዳዳቸው በ20 ሺሕ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር የተለቀቁት ባለፈው ዐርብ ታኅሣሥ 1፣ 2014 መሆኑን ቢቢሲ የሶማሌ ክልል የጋዜጠኞች ማኅበርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ ለጋዜጠኞቹ የዋስትና ገንዘቡን ማለትም በአጠቃላይ 80 ሺሕ ብር ያስያዘው ማኅበሩ ነው፡፡

የሶማሌ ጋዜጠኞች ማኅበር አባላቱን ከእስር ለማስፈታት ለዋስትና የሚያስፈልጋቸውን 80 ሺህ ብር ከከተማው ባለሐብት ተበድሮ በመክፈል እንዲለቀቁ ማድረጉንም ፕሬዝዳንቱ አያን ሽኩሪ ዑስማን መናገራቸው ተመላክቷል፡፡

ቢቢሲ ለአቶ አያን የጋዜጠኞቹ አሰሪ ጋዜጠኞቹ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የቀረበባቸውን ክስ አስመልከቶ ያሉ ወጪዎችን ሊሸፍን ሲገባው እናንተ እንዴት የጠበቃ እና የዋስትና ወጪዎችን ለብቻችሁ ልታወጡ ቻላችሁ የሚል ጥያቄ አቅርቤላቸው ‹‹እንደ ሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማኅበር ማንኛውም ጋዜጠኛ ግዴታውን እንደሚወጣው ሁሉ መብታቸውን የማስከበር ግዴታ አለብን። ስለዚህ መርጠን ያደረግነው ሳይሆን ግዴታችንን ነው የተወጣነው›› እንዳሉት አስነብቧል፡፡

በቀድሞዋ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን ዐብዱላሂ ባለቤትነት ስር እንደነበረ የሚነገረው ነበድ ቴሌቪዥን ተዘግቶ ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ጣቢያው ባሰራጨው የፕሮግራም ይዘት ምክንያት እንደነበር መነገሩ አይዘነጋም፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያውን መዘጋት ተከትሎ ከጋዜጠኞቹ በተጨማሪ በተመሳሳይ የወይዘሮ ፊልሳን አባት አቶ ዐብዱላሂ በቁጥጥር ስር ውለው ወዲያውኑ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡

የቀድሞዋ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን ዐብዱላሂ የመንግሥት ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ያስታወቁት ከአዲሱ መንግስት ምሥረታ አንድ ሳምንት ቀድሞ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img