– በመንግሥት በኩል እስካሁን የተሠጠ ምላሽ የለም
አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 4፣ 2014 ― መከላከያን ጨምሮ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከቀናት በፊት በቁጥጥር ስር ካዋሏት የላሊበላ ከተማ ለቀው መውጣታቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እና ሬውተርስ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል፡፡
ይህንኑ ተከትሎም የሕወሓት ኃይሎች ያለ ምንም ተኩስ ከተማዋን ዳግም መቆጣጠራቸውን የዜና ወኪሎቹ የዓይን እማኞችን ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡
ሬውተርስ አንድ የዓይን እማኝ ነግሮኛል እንዳለው፣ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላሊበላን የለቀቁት ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ነበር፡፡
የዓይን እማኙ ‹‹የመንግሥት ኃይሎች ጥምረት የመጨረሻዎቹ ወታደሮች እሁድ ጠዋት ሲወጡ ነበር። ከርቀት የተኩስ ድምጽ እንሰማ ነበር። ነገር ግን የሕወሓት ኃይሎች ከተማዋን የተቆጣጠሩት በከተማዋ አንዳችም የተኩስ ልውውጥ ሳይደረግ ነው›› ሲሉ አክለዋል፡፡
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በበኩሉ አንድ የዐይን እማኝን ጠቅሶ እንደዘገበው በርካታ የላሊበላ ነዋሪዎች በቀልን በመፍራት ከተማዋን ለቀው ሸሽተው ወጥተዋል። የበቀል ፍርሃቱ የመንግሥት ኃይሎች ከተማዋን ከአማጺያኑ አስለቅቀው ሲቆጣጠሩ ደስታችንን በመግለጻችን ነው ብሏል።
የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የላሊበላን ከተማ ለቀው ወጥተዋል ስለመባሉም ሆነ የሕወሓት ኃይሎች ዳግም ከተማን ተቆጣጥተዋል ስለተባለው መረጃ ከመንግስት በኩል የተሰጠ መረጃ የለም፡፡
የሕወሓት ኃይሎች በአንጻሩ ሰፊ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ በመክፈት ከላሊበላ በተጨማሪ ጋሸናን በድጋሚ መቆጣጠራቸውን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
የላሊበላ ከተማ በዓለም ቅርስነት የተያዙ አብያተ ክርስትያናት የሚገኙባት ታሪካዊ ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡