Sunday, September 22, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት ሁኔታዎች ሲሻሻሉ በደሴ እና ኮምቦልቻ የተቋረጠው ድጋፍ ይቀጥላል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 1 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአማራ ክልል ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚገኙት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘኖች መዘረፋቸውን ተከትሎ እርዳታ ማቋረጡን መግለጹ ይታወቃል፡፡

በዛሬው እለት የተባበሩት መንግታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ማስተባበሪያ ከመንግስት ጋር በጋራ በሰጠው መግለጫ በኮምቦልቻ እና ደሴ ከተሞች የነበሩት መጋዘኖች በሕወሓት ኃይሎች መዘረፉን በማረጋገጥ፣ ነገሮች ሲሻሻሉ ድጋሚ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የቢሮው እና የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ኃላፊ ዶ/ር ካትሪን ሶዚ በዛሬው መግለጫቸው፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ መጋዘኖች እንዴት እንደተዘረፉ አስረድተዋል፡፡ ሰራተኞቹ በዛቻ እና ማስፈራሪያ እንዲሁም ጠብመንጃ ተደቅኖባቸው እንደነበር ያስታወሱት አስተባባሪዋ፣ በዚሁ ሰበብ የመጋዘኖቹን ዝርፊያ ማስቆም አልቻሉም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ለትግራይ ክልል ቶሎ ቶሎ እርዳታ እንዲደርስ ደጋግሞ የሚያሳስበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ‹‹የአፋር እና የአማራ ክልሎችን ዘንግቷል›› በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ፤ ተመድ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩል ዐይን እንደሚመለከት መናገራቸውን አል ዐይን ዘግቧል፡፡

ጦርነቱ በአማራ ክልል 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ በአፋር ክልል ከ500 ሺ በላይ እንዲሁም በትግራይ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን መጉዳቱን ገልጸው ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 400 ሺ የሚሆኑት ለከፋ የምግብ ችግር መጋለጣቸውንም አስተባባሪዋ ይፋ አድርገዋል፡፡

በአንጻሩ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው፣ መንግስት በአፋርና በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን እየደገፈ ነው ያሉ ሲሆን፣ እርዳታ ሰጭ ተቋማት የሚያስፈጽሙት ‹‹የለጋሾቻቸውን ፍላጎት ብቻ ነው›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ ‹‹በህወሓት ምክንያት አምስት ጊዜ የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ›› ያሉት ኮሚሽነር ምትኩ፣ ቡድኑ ዜጎችን ከአላማጣ እስከ ደብረብርሃን ማፈናቀሉን ተናግረዋል፡፡ አቶ ምትኩ አያይዘውም ቡድኑ እርዳታን እንደጦር መሳሪያ መጠቀሙን ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img