Sunday, July 7, 2024
spot_img

የሕወሓት ኃይሎች በቆቦና ጭና ቢያንስ 49 ንጹሐንን መግደላቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ ይፋ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 1 2014 የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ቆቦና ጭና በተባሉ አካባቢዎች ቢያንስ 49 ንጹሐንን መግደላቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች አዲስ ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

የመብቶች ተቋሙ በሁለቱ አካባቢዎች በንጹሐን ግድያው የተፈጸመው ባለፈው ዓመት ከነሐሴ 25 አስከ ጳጉሜ 04፣ 2013 በነበሩት አስር ቀናት ውስጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ግድያውን ፈጽመዋል የተባሉት ኃይሎች ነሐሴ 25፣ 2013 ጭና ወደተባለችው መንደር በመግባት ከመከላከያ እና ከአማራ ክልል ኃይሎች ጋር ውጊያ ካካሄዱ በኋላ ቦታውን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት በነበሩ አምስት ቀናት በ15 የተለያዩ ስፍራዎች 26 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎች መናገራቸውን ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት በተመሳሳይ በዚያው ክልል በምትገኘው በቆቦ ከተማ ጳጉሜ 4፣ 2013 በአራት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የሕወሓት ኃይሎች 23 ሰዎችን እንደገደሉ የዓይን ምስክሮችን ዋቢ አድርጎ አመልክቷል፡፡ ይህ ግድያ የአካባቢው አርሶ አደሮች በሕወሓት ኃይሎች ላይ ለፈጸሙት ጥቃት የወሰዱት የበቅል እርምጃ ነው ብሏል።

ከዚህ አጋጣሚ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ያሰፈረው ሪፖርቱ፣ በሐምሌ አጋማሽ ላይ ቆቦን የተቆጣጠሩት የትግራይ ኃይሎች ጳጉሜ 4፣ 2013 ከቆቦ አቅራቢያ ወዳሉ መንደሮች በመሄድ መሳሪያ መፈለግ በጀመሩበት ጊዜ በአርሶ አደሮች ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ውጊያ ተካሂዶ ነበር ያለ ሲሆን፣ ኃይሎቹ ወደ ቆቦ ሲመለሱ እርሻቸው ላይ ሲሰሩ የነበሩ አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት ፈጽዋል ነው ያለው፡፡

በጭና እና ቆቦ ውስጥ የሕወሓት ኃይሎች በአጠቃላይ 49 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ያመለከተው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ የዓይን እማኞች ከሟቾቹ መካከል የ44ቱን ሰዎች ስም መጥቀሳቸውን ገልጧል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች በጉዳዩ ላይ ከሕወሓት መሪዎች አስተያየት ለማግኘት ያወጣውን ሪፖርት ቢልክም ምላሽ አላገኘሁም ብሏል፡፡

ድርጅቱ በመስከረም እና በጥቀምት ወር ላይ በጭና ተክለሐይማኖት መንደርና ቆቦ ከተማ ውስጥ ስለተካሄደው ውጊያና የተከሰተውን ለማወቅ ግድያዎቹን ያዩ እማኞችን፣ የሟች ዘመዶችንና ጎረቤቶችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 36 ሰዎችን ከርቀት ቃለ መጠይቅ ማድረጉን ገልጿል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img