Sunday, September 22, 2024
spot_img

ወደ ቢሮ የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከሱዳን በስተቀር የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎችን አነጋገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 30፣ 2014 ― ባለፉት ሁለት ሳምንታት በግንባር መከላከያን ለመምራት ዘምተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ወደ ቢሮ ሲመለሱ ከሱዳን በስተቀር የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎችን አነጋግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቅድሚያ ሰጥታ እየሠራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በትላንትናው እለት ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከዩጋንዳ፣ ከሶማልያ፣ ከኤርትራ እና ከደቡብ ሱዳን መሪዎች ጋር ጥልቅ የስልክ ውይይት አድርጌያለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ጠ/ሚሩ አያይዘውም ከአገራቱ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎችን ሲያነጋግሩ የዘለሏት ሱዳን፣ በቅርብ ጊዜያት በድንበር አካባቢ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ መሆኗ ይታወቃል፡፡

በድንበር አካባቢ ባለው ውዝግብ ከአስር ቀናት በፊት መንግስት በሱዳን በኩል ሰርገው የገቡ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች በኩል ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የሱዳን ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በአልፋሽቃ አካባቢ በተሰማራው የሱዳን ሠራዊት ላይ የኢትዮጵያ ጦርና ሚሊሻ ጥቃት ፈጽመዋል ብሎ ነበር፡፡ ሆኖም የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ፣ የሱዳን ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል መባሉ ፍጹም ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የኢፌዴሪ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ በወቅቱ ከሱዳን በኩል የቀረበውን ክስ በማጣጣል፣ ‹‹ኢትዮጵያ ጥቃት የምትፈጽምበት ምክንያት የለም›› ሲሉ ለኢሳት ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል የድንበር ውዝግብ እንዳለ ያስታወሱት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ይህ በሕጋዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት አመልክተው፣ ‹‹መሬታችን በሰላም፣ በሕግና በድርድር ይመለሳል ብለን ስለምናስብ፣ በዚህ ወቅት ሱዳንን የምናጠቃበት ሁኔታ ላይ አይደለንም›› ብለዋል።

ከዚህ በተቃራኒው ከሱዳን በኩል የመተናኮል ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ኤታማጆር ሹሙ፣ ከሱዳን በኩል ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንደሚደረግና ‹‹የሕዳሴው ግድብ ግንባትን ለማደናቀፍ እየሰራች መሆኑን እናውቃለን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹እነሱ የላኳቸው ኃይሎች እየመጡ እየደመሰስናቸው ነው። የራሳችንን ተላላኪዎች መደምሰስ እንጂ ለምን ትልካላችሁ ብለን ከእነሱ ጋር ውዝግብ፣ ግጭትም ሆነ ጦርነት ውስጥ መግባት አንፈልግም›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን አል ፋሻቃ በሚባለው ለም መሬት አካባቢ ለረዥም ጊዜ የቆየ ውዝግብ ውስጥ እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img