አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 29፣ 2014 ― የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን በግንባር ለመምራት ወደዚያው አቅንተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያውን ምእራፍ አጠናቅቄ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ቢሮ መመለሴን እወቁት ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ዘምተው መከላከያን እንደሚመሩ ያስታወቁት ኅዳር 13፣ 2014 ሲሆን፣ ያለፉትን 16 ቀናት በግንባር እንደነበሩ ተነግሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ቢሮ መመለሳቸውን በገለጹት ማስታወሻ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት ጠላቶቻችን ጉልበታቸው ዝሎ፣ የጥላቻና የጠበኝነትነ መንገድ ጥለው፣ የፍቅርን እና የሰላምን መንገድ እስኪመርጡ ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መከላከያን ከግንባር ሆነው መምራት እንደጀመሩ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ በሕወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩት የሰሜን ሸዋ፣ የአፋር እንዲሁም በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡