Tuesday, October 15, 2024
spot_img

ጉምሩክ በተመላላሽ ነጋዴዎች ላይ የጣለው አዲስ ክልከላ የበርካታ ዜጎችን የእንጀራ ገመድ የሚቆርጥ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 28፣ 2014 ― የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ የገቢ ዕቃዎች ክልከላና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከተለያዩ አገራት አልባሳትና ጫማን ጨምሮ ወደ ሀገር ይዘው የሚገቡ ተመላላሽ ነጋዴዎች ምንም ዐይነት እቃ ይዘው እንዳይገቡ መከልከሉን ትላንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ የክልከላው ምክንያት በተመላላሽ መንገደኞች ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ነገር ግን ለንግድ አላማ እየዋሉ የሚገኙ ዕቃዎች በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና በመፍጠራቸው መሆኑን ገልጧል፡፡

ነገር ግን ይህ የጉምሩክ ክልከላ በዚሁ ስራ የሚተዳደሩ በርካታ ተመላላሽ ነጋዴዎችን የእንጀራ ገመድ የሚቆርጥ ነው በሚል ቅሬታዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡

በጉዳዩ ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች በሰነዝሯቸው አስተያየቶች አዲስ የተጣለው ክልከላ በተለይ ከዱባይ እና ቻይና በሻንጣ እቃ ይዘው ወደ አገር ቤት በማስገባት ኑሯቸውን ከሚገፉ በርካታ ነጋዴዎች ጨምሮ፣ እቃዎች በሚጫኑባቸው አገራት ሆቴል የሚያከራዩ፣ የቲኬት ሽያጭ ቢሮችን እና ተዛማጅ ጉዳዮችን በሚሠሩ ዜጎች ላይ ሁሉ ተያያዥ ጉዳት እንደሚያስከትል ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ የገቢ ዕቃዎች ክልከላና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የደንበኞች ትምህርት ቡድን አባል የሆኑት አቶ ምትኩ አበባው በአንጻሩ የክልከላውን ምክንያት ሲያስረዱ ‹‹አንድ መንገደኛ ያለቀረጥ ሁሌም እየተመላለሰ እቃ የሚያመጣ ከሆነ በህጋዊ መልኩ በኮንቴነር የሚያስጭኑና ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎችን ኪሳራ ዉስጥ የሚያስገባና ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው›› ብለዋል፡፡

ክልከላውን ተከትሎ አስተያየት ከሰነዘሩት መካከል የሆኑት ፖለቲከኛና የምጣኔ ሐብት ባለሞያው አቶ ሙሼ ሰሙ፣ የመንግስት አንዱና ዋነኛው ተግባር ዜጎች ሰርተው የሚኖሩበት ሁኔታዎች ማመቻቸትና እድል መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም መንግስት ራሱ የስራ እድል መፍጠርም ሆነ በግል ዘርፉ አማካኝነት ስራን ማመቻቸት ካልቻለ፣ ዜጎች ለእርዳታ ተቀባይነትና ለማህበራዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ ሲባል ኢ- መደበኛ ስራዎችን ቢቻል ከታክስ ነጻ በማድረግ ወይም በጣም በዝቅተኛ ታክስ ሰርተው የመኖር እድል ሊነፍጋቸው አይገባም ሲሉ መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

ይህ ጉዳይ ከጎረቤት ጀምሮ በብዙ ሀገሮች የተለመደ ነው ነው ያሉት አቶ ሙሼ፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎቿ የስራ እድል መፍጠር እንደሚጠበቅባትም አስታውሰዋል፡፡

ይህ ነባራዊ ሀቅ ባለበት ሁኔታ ተቆጥረው በገደብ እንዲገቡ በሕግ የተፈቀዱ አልባሳትና ቁሳቁሶችን ‹‹እጅግ ፈታኝ በሆነ መንገድ ጥሪት አብቃቅተው ትንሽ ትርፍ ለማግኘት ከሚበላ፣ ከሚጠጣና ከትራንስፖርት ቆጥበውና ተዳብለው እያደሩ ቤተሰቦቻቸውን ዳቦ ለማብላት የሚታገሉ›› ያሏቸው በተለምዶ የሻንጣ ሰራተኛ የሚባሉትን ‹‹በዚህ ፈታኝ ጊዜ ስራቸውን ማገድ›› ስራ አጥነትን በማባባስ ማህበራዊ ቀውስንና ሁከት ከመቀስቀስ ውጭ ትርፍ የለውም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ውሳኔውን ያሳለፈው ጉምሩክ ክልከላውን ተከትሎ ማንኛውም መንገደኛ ከቀረጥ ነጻ ይዞ እንዲገባ የተፈቀዱ አልባሳትና ጫማዎችን ጨምሮ ዕቃዎችን ተገቢውን ቀረጥና ታክስ መክፈል እንደተጠበቀ ሆኖ ለንግድ እላማ የሚውል ነው ተብሎ ከታመነ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅጣት ይስተናገዳል ያለ ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ይዞ የሚመጣ ከሆነ ግን በወንጀል መጠየቅ ድረስ የሚያስደርስ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img