Saturday, September 21, 2024
spot_img

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሰበብ ከ45 ሺሕ በላይ መምሕራን ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ማኅበሩ አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 28፣ 2014 ― የፌደራል መንግሥት ከሕወሓት ኃይሎች ጋር እያካሄደው ባለውና አንድ ዓመት በተሻገረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ቢያንስ 45 ሺሕ መምሕራን ከሥራ ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ በመላ አገሪቱ ከ600 ሺሕ በላይ አባላት እንዳሉ የሚነገር ሲሆን፣ በጦርነቱ ሰበብ ያለ ሥራ የተቀመጡና በችግር ውስጥ የሚገኙ የመምሕራን ብዛት ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ነግረውኛል ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

ጦርነቱ ከተከሰተ ጀምሮ በነበሩበት አካባቢ መቀጠል ባለመቻላቸው በርካታ መምህራን ከአማራ፣ ከአፋርና ከትግራይ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተዘዋውረው እንዲሠሩ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ማኅበሩ ጥያቄውን ተቀብሎ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡

ይሁን እንጂ ችግሩ ከማኅበሩ አልፎ ከአገር አቅም በላይ ስለሆነ፣ በርካታ ፍላጎቶች ቢቀርቡም፣ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር የመፍትሔ ሐሳቦችን ከማፈላለግ ውጪ የተለየ ነገር ማድረግ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የመምህራን ደመወዝ ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ተመልሶ እንዲከፈላቸውም ከየክልሎቹ የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በኅዳር ወር መገባደጃ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጸው፣ በጦርነቱ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ300 በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸው ተገልጿል፡፡

 በሌላ በኩል በአገር አቀፍ ደረጃ ጦርነቱ እያመሳቸው በሚገኙ አካባቢዎች ከሥራ ገበታቸው የተስተጓጎሉና የተለያየ ዓይነት ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች ምን ያህል እንደሆኑ በቅርቡ ጥናት እንደሚጀምር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የደረሰውን የጉዳት መጠን በቁጥር ለይቶ መግለጽ እንደማይችል የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን የደረሰውን ጊዜያዊ መረጃ ለማጠናቀር ከሠራተኞች ፌዴሬሽኖች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጦርነቱ ሁኔታ መፍትሔ ባገኘ ማግሥት በሚያደርገው ጥናት የሚገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት እንዴት ማቋቋም እንደሚገባ፣ የደረሰውን ኪሳራ በምን ሁኔታ መደገፍ እንደሚቻል ከመንግሥት ጋር እንደሚሠሩ አቶ ካሳሁን አክለው ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img