Thursday, November 28, 2024
spot_img

በአርሲ ዞን ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት የሸኔ አባል ነኝ ብሎ እጅ መስጠት የተለመደ ተግባር እየሆነ መምጣቱ ተነገረ

  • የዞኑ አስተዳዳሪ ስለ ጉዳዩ ምላሽ ሰጥተዋል

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 27፣ 2014 ― በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን ወጣቶች የኦነግ ሸኔ አባል ሳይሆኑ እንደሆኑ በመግለጽ፣ የክልሉን መንግሥት በማጭበርበር ወደ ካምፕ በመግባት ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ስማቸው ያልጠቀሳቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ከክልሉ መንግሥት በሚቸራቸው የተለያየ ጥቅማጥቅም የተነሳ፣ በአርሲ ዞን ዙሪያ የሚኖሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ራሳቸውን የኦነግ ሸኔ አባል በማስመሰል ለክልሉ መንግሥት እጅ እየሰጡ ይገኛሉ። ግለሰቦቹ ለመንግሥት እጅ ይስጡ እንጂ፣ በአካባቢው በነጻነት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ነው የተነገረው።

እጅ በመስጠታቸው ጥቅማ ጥቅም ከክልሉ መንግሥት ስለሚያገኙ በሊስትሮ እና በተለያየ የንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጭምር፣ “ኦነግ ሸኔ ነን” እያሉ በመመዝገብ ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሙሳ ሴሪ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አባ ገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች ባለማወቅ ኦነግ ሸኔን የተቀላቀሉ የክልሉ ወጣቶችን እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። አስተዳዳሪው እንደሚሉት በተደጋጋሚ ጥሪ የሚደረገው፣ የኦነግ ሸኔ ቡድኖች ከጥፋታቸው እንዲመለሱ፣ የአካባቢው ወጣቶች ሸኔን እንዳይቀላቀሉ፣ መረጃ በመስጠት እንዲሁም የቁሳቁስ (ሎጂስቲክ) ዕርዳታ በማድረግ ሸኔን እንዳይተባበሩ ለማድረግም ጭምር ነው።

ኃላፊው አክለውም፣ የሸኔ አባላት በአርሲ በሦስት ዞኖች መካከል የሚገኝ ረጅም ርቀት ያለው ጫካ ውስጥ እንዳሉ እና በርካታ ዘግናኝ ጥፋት እየፈጸሙ እንደሚገኝም አሳውቀዋል። አቶ ሙሳ ከኅዳር 19 እስከ 21፣ 2014 ባሉት ቀናት ብቻ 15 ወጣቶች ጥፋታቸውን አምነው ተመልሰዋል ያሉ ሲሆን፣ በቀጣይም ብዙዎች ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ወጣቶች እራሳቸውን የሸኔ አባል አድርገው እያቀረቡ ነው ስለተባለው ጉዳይ፣ “ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ የሚለው፣ የበሬ ወለደ እና ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው” በማለት አስተዳዳሪው ጉዳዩን አስተባብለዋል። አክለውም፣ ከዞኑ ዕውቅና ውጪ እንደዚህ ዓይነት ተግባር እንዲፈጸም የሚያደርጉ ኃላፊዎች ካሉ፣ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎባቸው ለሕግ እንደሚቀርቡ መናገራቸው ተመላክቷል፡፡

በመንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚባለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚለው ቡድን በኦሮሚያ የተለያዩ አካባዎች በንጹሐን ለሚደርስ ግድያ በመንግስት ተጠያቂ የሚደረግ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img