- ትምኒት የፌስቡክ ኩባንያ አርቲፊሻል ኢንተሌጀንስ አሠራር በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለሚታየው የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ባለው አስተዋጽዖ ላይ ምርምር የማድረግ ሐሳብ እንዳላት ገልጻለች
አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 25፣ 2014 ― የቀድሞ የጉግል ኩባንያ ተመራማሪ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ትምኒት ገብሩ የራሷን የአርቲፊሻል ኢንተሌጀንስ የምርምር ተቋም ማቋቋሟ ይፋ ተደርጓል፡፡
እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘግባ ከሆነ ትምኒት ያቋቋመችው የምርምር ተቋም ዓላማ ከግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተጽዕኖ ነጻ የሆነ እና የግዙፍ ኩባንያዎች አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መድልዖ የሚያደርጉቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጠቅም ምርምር ማካሄድ ነው፡፡
ትምኒት ለቢቢሲ በሰጠችው ቃል ደግሞ የትምህርት ተቋማት ለተመራማሪዎች ዝግ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ‹‹ማጭበርበር እና ብዝበዛ የሞላባቸው›› እንደሆነም ጠቁማለች፡፡
አያይዛም ተቋማቱ ሥልጣን ላይ ያሉ አካላትን ለማስደሰት ስለሚሠሩ፤ አማራጭ ድምጾችን እና ለየት ያሉ አስተሳሰቦችን የመጨፍለቅ አዝማሚያ እንደሚያሳዩ አክላለች፡፡
ከኤርትራውያን ቤተሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደችው ትምኒት ገብሩ፣ የፌስቡክ ኩባንያ አርቲፊሻል ኢንተሌጀንስ አሠራር በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለሚታየው የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ባለው አስተዋጽዖ ላይ ምርምር የማድረግ ሃሳብ እንዳላት ገልጻለች፡፡
የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሰው ሠራሽ ልኅቀት የሚገጥማቸውን ችግር የሚያጠናውና ለለውጥ ንቅናቄ የሚያደርገው የትምኒት አዲስ ድርጅት፣ ዲስትሪብዩትድ አርቲፊሻል ሪሰርች ኢንስቲትዩት ይሰኛል፡፡
ዶ/ር ትምኒት ገብሩ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እጅግ ትኩረትን ባገኘው በሰው ሰራሽ ልህቀትና ተያያዥ በሆነው የሥነ ምግባር ዘርፍ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈች ተመራማሪ ናት፡፡
ትምኒት ቀድሞ በምትሠራበት ጎግል ‹‹ትኩረት የተነፈጋቸው ድምጾችን ያፍናል›› በማለት ለሥራ ባልደረቦቿ የኢሜል መልዕክት መላኳን ተከትሎ ከሥራ ካባረራት አንድ ዓመት ገደማ ሆኗል፡፡
ጉግል ትምኒትን ማባረሩን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጉግል ባልደረቦች ተቋሙን በዘረኝነትና መልዕክቶችን ቀድሞ በመመርመር (ሳንሱር) የሚከሰውን ደብዳቤ በመፈረም ከትምኒት ጎን መቆማቸው አይዘነጋም፡፡