Tuesday, October 8, 2024
spot_img

አሜሪካ በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸም አለመፈጸሙን የማወጅ እቅዷን አዘገየች

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 23፣ 2014 ― በትግራይ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ስታወጣ የቆየችው አሜሪካ፣ በጦርነቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸም አለመፈጸሙን የማወጅ እቅዷን አዘግይታለች፡፡

ዘ ናሽናል ኒውስ የተባለ ድረ ገጽ ይዞት በወጣው ዘገባ እንዳመለከተው፣ አገሪቱ በጦርነቱ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያደረገችውን አጠቃላይ የሕግ ግምገማ ያዘገየችው ለሚካሄዱ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች እድል ለመስጠት ነው፡፡

ይህንኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ረዳት ሚኒስትር የሆኑት ሞሊ ፊ በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ አሜሪካ ከሳምንታት በፊት ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ ማእቀብ ስትጥል ልክ እንደ አሁኑ ሁሉ ለዲፕሎማሲ በር ለመተው በሚል ማእቀቡን አዘግይቻለሁ እንዳለች አይዘነጋም፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን የማወጅ እቅዷን አዘግይታለች የተባለችው አሜሪካ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ልኡኳ ጄፍሪ ፌልትማን በኩል የፌዴራል መንግስት እና ሕወሓትን ለማደራደር እንቅስቃሴ ላይ መሆኗ ሲነገር ሰንብቷል፡፡

ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ የተገኙት ልዩ መልእክተኛዋ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የሕወሓት መሪዎችን ማነጋገራቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡

አንድ ዓመት በተሻገረው ጦርነት በጦርነቱ የተሳተፉ አካላት የፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመከተ በስፋት ሲጠበቅ የነበረው በኢሰመኮ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተደረገው ምርመራ ሪፖርት በጥቅምት ወር መገባደጃ ይፋ መደረጉ አይዘነጋም፡፡

በዚሁ ምርመራ ሪፖርት በትግራይ ግጭት የተሳተፉ ሁሉም አካላት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በግጭቱ ተሳታፊ አካላት በተለያየ መጠን ተፈጽመዋል ከተባሉት ጥሰቶች ውስጥ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ይገኙበታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img