አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 22፣ 2014 ― ተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በመንግስት ተመቷል በሚል ሐሰተኛ ወሬ እየተነዛ ነው ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መግለጫ የመጣው የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ትላንት ማክሰኞ በትዊተር ገጻቸው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ መመታቱን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ ባሰፈሩት ማስታወሻ የውሃ ኃይል ማመንጫን በመምታት ተጠያቂ ያደረጉት ‹‹እያበቃለት ነው›› ያሉትን የፌዴራል መንግስት ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ‹‹በመንግስት የተመታው የተከዜ ግድብ ሳይሆን ተከዜን ተሻግሮ ወረራ የፈፀመው የሽብር ቡድኑ ነው›› ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ሕወሓት የተከዜ ግድብ ላይ መንግስት ጉዳት አድርሷል ሲል የትላንትናው የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በተመሳሳይ ግድቡ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል በሚል ክስ ቢያቀርቡም፣ የፌደራል መንግሥቱ ሐሰት ነው ብሎ ነበር፡፡
ለአሁኑ የሕወሓት ክስ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ‹‹የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ሞያተኛ ባልሆኑ ሰዎች ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንዲሰራ ከተደረገ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል›› ያስታወሰ ሲሆን፣ ‹‹ሕዝብን ለማሸበር እና ዓለም አቀፍ ትኩረትን ለመሳብ›› በሚል ህወሓት ከግድቡ ውሃው ሊለቅ እንደሚችል ጠቁሞ በታችኛው ተፋሰስ ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች የ‹‹ጥንቃቄ አድርጉ›› መልእክት ሰዷል፡፡
188 ሜትር ርዝመት ያለው በተከዜ ወንዝ ላይ የተገነባው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ፣ በቁመት ከአፍሪካ ትልቁ እንደሚያደርገው ይነገርለታል።