አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 21፣ 2014 ― በአማራ ክልል ገረገራ በተሰኘ አካባቢ የሕወሓት ተዋጊዎች የ12 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ በርካታ ሴቶችን አስገድደው መድፈራቸውን የዘገበው ግሎብ ኤንድ ሜይል ጋዜጣ ነው፡፡
ጋዜጣው ከሰብአዊ መብት አጥኚዎች ጋር በጋራ እንዳደረገው በገለጸው ምርመራ የሕወሓት ተዋጊዎች የ12 ዓመት እድሜ ያላት ታዳጊን ጨምሮ በርካቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት አድርሰዋል ያለው ኃይሎቹ ሥፍራውን በተቆጣጠሩበት የነሐሴ ወር 2013 ነው፡፡
ተዋጊዎቹ ከላሊበላ በደቡብ ምእራብ አቅጣጫ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የሚርቀው ገረገራ ደርሰው ለአራት በመሆን የ12 ዓመት እድሜ ያላት ታዳጊ ላይ ያደረሱትን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ያደረሱት በአባቷ ፊት መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ልጁ በፊቱ የተደፈረችው አባት ለመከላከል ሙከራ ቢያደርግም፣ ድብደባ እንደፈጸሙበትና እንገድልሃለን በሚል እነንዳስፈራሩት ነው የተነገረው፡፡
በሥፍራው ተዋጊዎቹ በተመሳሳይ የ14 ዓመት ያላት ሌላ ታዳጊን ደፍረው ጫካ ጥለዋት መገኘቷን ጋዜጣው በምርመራ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በስፍራው እስከ መስከረም የመጀመሪያ ቀናት ድረስ መቆየታቸው የተነገረው የሕወሓት ተዋጊዎች ወደ አካባቢው በዘለቁ ጊዜ፣ ቀድመው እኛ የምንፈልገው ወንዶችን ነው፣ ሴቶችን አንነካቸውም ማለቷን የምታስታውሰው ምትኬ የተባለች ሴት፣ ሆኖም ጥቂት ቆይተው ሴቶችን ያለ ርህራሄ መድፈር መጀመራቸውን እንዲሁም ድብደባም መፈጸማቸውን መናገሯ በዘገባው ሠፍሯል፡፡
ግሎብ ኤንድ ሜይል የተደፈሩት ሴቶች ምን ያህል እንደሆነ ያልጠቀሰ ቢሆንም፣ በርካታ መሆናቸውን ከአካባቢዎች ነዋሪዎች መስማቱን ዘግቧል፡፡
በገረገራ የሕወሓት ተዋጊዎች ፈጽውታል የተባለውን የአስገድዶ መድፈር በተመለከተ፣ ጋዜጣው የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን የጠየቅኩ ቢሆንም፣ ምላሽ አልሰጡኝም ብሏል፡፡
ዓለም አቀፉ የመብት ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የሕወሓት ኃይሎች በተመሳሳይ ከገረገራ 50 ኪሎ ሜትር በሚርቀው ንፋስ መውጫ ከተማ 16 ሰሴቶች የመደፈር ጥቃት አድርሰዋል ማለቱ መነገሩ አይዘነጋም፡፡