Sunday, September 22, 2024
spot_img

በእንግሊዙ ቴሌግራፍ ጋዜጣ የተሳሳተ ዘገባ ተሠራጭቶብኛል ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምላሽ ሰጡ

 – ንግግሩ በዩትዩብ ጥላቻ ያዘለ ነው በሚል እንዲነሳ ተደርጓል

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 20፣ 2014 ― በእንግሊዙ ቴሌግራፍ ጋዜጣ የተሳሳተ ዘገባ ተሠራጭቶብኛል ያሉት የቀድሞው የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቅርበት አላቸው የሚባሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለጋዜጣው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ምላሽ በሰጡበት ዘገባ፣ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መከላከያን ከጦር ግንባር ለመምራት ማቅናታቸው መነገሩን ተከትሎ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም በተመሳሳይ በግንባር ተገኝተው በሕወሓት ላይ ሊወሰድ ይገባል ያሉትን እርምጃ ያደረጉትን ንግግር ጠብ ጫሪ ነው ብሎታል፡፡

በኢህአዴግ/ሕወሓት አገዛዝ ዘመን በሽብር ወንጀል ሁለት ጊዜያት ክስ ተመስርቶባቸው በዕድሜ ይፍታህ እና በሞት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በግንባር ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ከፌዴራል መንግስት ጋር እየተዋጉ ያሉ የሕወሓት ኃይሎችን ‹‹ያለምንም ርህራሄ፣ ያለ ምንም አማራዊ/ኢትዮጵያዊ ደግነት አረመኔያዊ በሆነ ጭካኔ ነው ልንጋፈጣቸው የሚገባው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ጋዜጣው በዘገባው አናገርኳቸው ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ለዘር ማጥፋት የሚያነሳሳ ነው ያሉትን ንግግር በተመለከተ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በጻፉት ምላሽ፣ ከ800 ኪሎ ሜትሮች በላይ አቆራርጦ በደረሱበት ሁሉ አረመኔያዊ ወንጀሎችን ፈጽሟል ያሉትን የሕወሓት ወይም የሕወሓት መከላከያ ኃይል ‹‹እኛ ተጠቂዎቹ መፋለማችን በፈጣሪ የተሰጠን መብት ነው›› ብለዋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ዊንስተን ቸርችል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወራሪው ጀርመን ብሪታንያን በወረረበት ወቅት ‹የትኛውንም መንገድ ተጠቅመን ራሳችንን እንከላከል› የሚል ጥሪ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ እርሳቸውም ናዚን አርአያ አድርጓል ያሉት የሕወሓት ኃይል ወደተወለድኩበት የሸዋ አካባቢ እየመጣ መሆኑን ተከትሎ ያደረጉኹት ንግግር ከቸርችል ጥሪ የተለየ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአንጻሩ የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ሕዝብ ላይ በይፋ የዘር ጭፍጨፋ አውጀዋል ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፣ የጋዜጣው ሪፖርተር ላይ በተመሳሳይ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የእንግሊዝ አገር ዜግነት ያላቸው የቀድሞው የግንቦት ሰባት ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያደረጉት ንግግር ከሰሞኑ በተመሳሳይ ከሚኖሩበት አሜሪካ አገር በተመለሱት አቶ ታማኝ በየነ የማኅበራዊ ገጾች ላይ ተሠራጭቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዩትዩብ የጥላቻ ንግግር ያዘለ ነው በሚል ከድረ ገጹ ላይ እንዲነሳ አድርጎታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img