Sunday, October 6, 2024
spot_img

ባልደራስ አመራሮቹን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት ሲያቀኑ ታስረዋል ያላቸው አባሎቹ እንዲለቀቁ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 20 2014 ― ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) ከሰሞኑ አመራሮቹን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት ሲያቀኑ ታስረዋል ያላቸው አባሎቹ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡

ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መልለጫ እስረኞችን ለመጠየቅ የሄዱ ሰዎችን ማሰር በመደበኛም ሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊሳበብ የሚችል አይደለም ብሏል፡፡

ይህን መሰሉ ህገ ወጥነት ሲል የገለጸው ተግባር ‹‹ህዝብን በመከፋፍል ከጦርነት ባላነሰ መልኩ ሀገርን የሚጎዳ መሆኑ ግልጽ ነው›› ያለው ፓርቲው፣ የታሠሩ አባሎቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል በታሪክ ኢትዮጵያ ባጋጠሟት ወሳኝ ጦርነቶች መሪዎች ወደ ዘመቻ ሲሄዱ የበደሉት ካለ ይቅርታ ጠይቀው፣ አላግባብ ያሠሩትም ካለ ፈትተው፣ ሁሉን መርቀው ወደ ጦር ግንባር የሚሸኙበት አኩሪ ትውፊት ያለን መሆኑን አስታውሷል፡፡ ፓርቲው አያይዞም ‹‹ድላችንን በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ መስዋዕትነት እንድንጎናፀፍ፣ ፈጣሪም ለቂም በቀል ያልተነሳን መሆኑን ተገንዝቦ ለድል እንዲያበቃ፣ ‹‹መንግሥት ቂም በመያዝ›› አስሮታል ያለውን አቶ እስክንድር ነጋን እና ሌሎች የባልደራስ ፓርቲ አመራር አባላትን ጊዜ ሳይወስድ በመፍታት ለአገራቸው ሰላም አስተዋጽኦ ያድርጉ ብሏል፡፡

ፓርቲው በዚሁ መግለጫው የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ‹‹ውድ የህይወት ዋጋ በመክፈል ላይ ይገኛሉ›› ላላቸው የአማራ እና የአፋር ልዩ ኃይሎችን ጨምሮ ለፋኖ እና ለሚሊሺያ ተገቢው ስንቅና ትጥቅ ማቅረብ ይገባል ብሏል፡፡

ባልደራስ ጨምሮም በተለይ ‹‹በአማራ ክልል ያለውን ህዝባዊ ኃይል በጥርጣሬ የማየቱ ሁኔታ ስላልተወገደ አቅርቦቱ እየተጓተተ ሰለመሆኑ ቅሬታዎች›› እንዳሉ እንደሚሰማ አስታውቋል፡፡

ጦርነቱ ዓለም አቀፋዊ መልኩ እየጎላ መምጣን የገለጸው ባልደራስ፣ ‹‹በአንድ መልኩ ለኢትዮጵያዊው ኃይል የሚሰጠው ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች›› የኢትዮጵያ ጠላት ነው ላለው ሕወሓት ላይ ‹‹በሃገራዊ አንድነት መንፈስ ምልዐተ ህዝቡን ከማስተባበር አንጻር እንጂ የፖለቲካ ትርፍን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን አይገባም›› ብሏል፡፡

በመሆኑም ፓርቲው ለዚህ ‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው ለማታውቀው›› ላለው ትግል የሚካሄደው መነሳሳት እና የሚደረገው ድጋፍ ለሃገረ ኢትዮጵያ እንጂ ለፓርቲ አለመሆኑን ተገንዝቦ በሆደ ሰፊነት ሁሉንም ሀገር ወዳድ ኃይሎች ማስተባበር እንደሚያስፈልግ ገልጧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img