Saturday, October 12, 2024
spot_img

በአፋር ክልል ጭፍራ ከተማ በነበረ ጦርነት መስጂዶች ሆን ተብሎ እንዲወድሙ ተደርጓል ተባለ

– ‹‹የሕወሓት ተዋጊዎች በመስጂዶች ላይ ውድመት ከማድረሳቸው በተጨማሪ ወደ ውስጥ በመዝለቅ አስካሪ መጠጦችን ሲጠጡ እንዲሁም ሲጨፍሩ ታይተዋል›› ሐሩን ሚዲያ አነጋገርኳቸው ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 20 2014 ― በአፋር ክልል ጭፍራ ከተማ በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት ኃይሎ መካከል በነበረው ጦርነት መስጂዶች መውደማቸውን የአልጀዚራ ዐረብኛ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ጭፍራ ከተማ ባለፉት ጊዜያት ድንበር ጥሶ በገባው የሕወሓት ኃይል ቁጥጥር ስር የነበረ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ በትላንትናው እለት የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአፋር ልዩ ኃይል እንደተቆጣጠራት የመንግስት መገናኛ ብዙኃን እና አልጀዚራ ዘግበዋል፡፡

አልጀዚራ በዘገባው በሥፍራው በነበረው ጦርነት በጎዳናዎች ላይ በርካታ አስከሬን እንደሚታይ ያመለከተ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በጭፍራ ከተማ የንግድ ሱቆች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድመዋል ብሏል፡፡ ዘገባው አያይዞም በጦርነቱ መስጂዶችም ጭምር ከውድመት አለመትረፋቸው ጠቁሟል፡፡

በአፋር ክልል ባሉ አካባቢዎች መስጂዶቹ ላይ የደረሰውን የመስጂድ ውድመት በተመለከተ አልጀዚራ ጥቃቱን አድራሹ ማን እንደሆነ የገለጸው ነገር ባይኖርም፣ ሐሩን የተባለ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ጥቃቱን ያደረሱት የሕወሓት ኃይሎች ናቸው፡፡

እንደ ሐሩን ሚዲያ ዘገባ የሕወሓት ተዋጊዎች በመስጂዶች ላይ ውድመት ከማድረሳቸው በተጨማሪ ወደ ውስጥ በመዝለቅ አስካሪ መጠጦችን ሲጠጡ እንዲሁም ሲጨፍሩ ታይተዋል ብሏል፡፡ ዘገባው አክሎም ኃይሎቹ ቁርኣን ማቃጠላቸውንም አመልክቷል፡፡

ከገለልተኛ ወገን የጉዳቱን አድራሽ አካል ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ መስጂዶችን በማውደም የተወነጀለው ሕወሓትም ቢሆን በጉዳዩ ላይ እስከአሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡

አንድ ዓመት የተሻገረው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ኃይሎች ጦርነት በቅርብ ቀናት ተባብሶ ቀጥሎ ጠቅለላ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመውረድ መከላከያን እየመሩ መሆናቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img