Sunday, July 7, 2024
spot_img

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገር ላይ ክህደት በመፈፀም በሚስጢር ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል ያላቸውን ግለሰቦች ዲግሪ ሊነጥቅ እንደሚችል አስጠነቀቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 17፣ 2014 ― በኢትዮጵያ አንጋፋ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር አፍራሽ ሽብርተኞች ጋር ሲተባበሩ በሀገር ላይ ክህደት በመፈፀም በሚስጥር ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል ያላቸውን ጥቂት ግለሰቦች ዲግሪ ሊነጥቅ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባወጣው መግለጫ ‹‹ከሀገር አፍራሽ ሽብርተኞች ጋር ሲተባበሩ በሀገር ላይ ክህደት በመፈፀም በሚስጥር ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል›› ያላቸውን ግለሰቦች አልጠቀሰም፡፡

ሆኖም ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት እና ጥናት ታዋቂ የሆኑት የዩኒቨርሲቲው መምህራኖቹ ፕሮፌሰር አሰፋ ፍስሐ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ረዳኢ በአስቸኳይ ጊዜ እዝ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሮ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፌስቡክ ባሰራጨው መረጃ የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አባላት በዛሬው እለት በመሰባሰብ በኢትዮጵያ እየታየ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን አሳውቋል፡፡

በፕሬዝዳንቱ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተነቧል በተባለው በዚህ የአቋም መግለጫ የዩኒቨርሲቲው ውለታ ያለባቸው ለቀድሞ እና ለአሁን ምሁራን መልእክት ተላልፏል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ለምሁራኑ በሰደዱት መልእክት ‹‹የጀመራችሁትን ሀገር የማዳን ትግል ዩኒቨርሲቲው የሚደግፍ መሆኑን አውቃችሁ እስከመጨረሻው ድረስ እንድትፋለሙ›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ይዞታል ያለውን የተዛባ ግምገማና አላስፈላጊ የውስጥ ጣልቃ-ገብነት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይሰራጫል ያለውን ሐሰተኛ ዜና አውግዟል፡፡  

በሌላ በኩል አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ህወሓትን በግልጽ ስለሚደግፉ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰበው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መግለጫ፣ የአሜሪካ ህዝብና መንግስት በተሳሳተ መረጃና ሆን ተብሎ በሚቀነባበር ሴራ ኢትዮጵያን ለማዳከም፣ አሸባሪውን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት በጥልቀት እንዲያስቡበት ሲል መክሯል፡፡

አያይዞም ለአንድ ሀገር ሉአላዊነት፣ ነጻነትና ፍትህ ለሚታገሉ ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰቦችና ሀገራት ለእውነተኛው ትግላችን “በቃ” ብለው ደጋፋቸውን እንዲያሳዩ እንዲሁም መላው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት፣ በአድሏዊ ማዕቀብና በሽብርተኝነት ላይ ጠንካራ ተቃውሞውን እንዲያሰማና ከእኛ ጋር በጋራ እንዲቆም ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአአዩ ማህበረሰብ አባላት የህልውና ያሉትን ዘመቻ ከግቡ ለማድረስ የመንግስትን ጥሪ በሙሉ በመቀበል አስፈላጊ ከሆነ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img