አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 17፣ 2014 ― ከማክሰኞ ኅዳር 14፣ 2014 ጀምሮ ከግንባር መከላከያን እየመሩ መሆናቸው የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በዛሬው እለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመንግስት መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር በየት ግንባር ተገኝተው እየመሩ መሆናቸው ባይገለጽም፣ ‹‹ከጀርባዬ የምታዩት ጠላት እስከ ትላንት ድረስ የተቆጣጠረው ተራራ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አሁን ካሳ ጊስታን ይዘናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዛሬ ጭፍራን እና ቡርቃን እንይዛለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተሩ በአንድ ቀን ያገኘነውን ድል አይታችኋል፣ ይኸው ይቀጥላል ያሉ ሲሆን፣ ጠላት ያሉት ኃይል ከመከላከያ ጋር ሊፎካከር የሚያስችል ቁመና እንደሌለውም ገለጸዋል፡፡
አክለውም ‹‹የኢትዮጵያ ነጻነት እስኪረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ማየት ነው፣ በድል እንደምናሳካው እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ መደበኛ የመንግስት ሥራዎችን ምክትል ጠቅላይ ሚኒትር ደመቀ መኮንን እየመሩት መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡