Saturday, October 5, 2024
spot_img

ምሥጢራዊ በተባለ የዙም ውይይት ተሳትፎ ያደረጉት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት አባሏ ማስተባበያ ሰጡ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 17፣ 2014 ― ባሳለፍነው እሑድ በአደባባይ የታወቁ ኢትዮጵያዊያን እና የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት በሕወሃት መሪነት በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ዙሪያ በምስጢር መወያየታቸውን ካናዳዊው ጋዜጠኛ ጀፍ ፒርስ በማኅበራዊ ትስስር ዘዴዎች ካሰራጨ በኋላ በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ይህን ውይይት የመሩት ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ሲሆኑ፣ ለተወያዮቹ ማብራሪያ በመስጠት የሕወሃት አባሉና በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እንተካለን በሚል በአሜሪካ ዋሺንግተን ጥምረት መመስረታቸውን ካስታወቁት ዘጠኝ አካላት መካከል የሆኑት አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከውጭ አገራት ዲፕሎማቶች መካከል በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ፣ አሜሪካዊቷ ዲፕሎማት ቪኪ ሀድልስተንን ጨምሮ በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ እንግሊዝና አውሮፓ ኅብረት የቀድሞ አምባሳደሮች ተሳትፈዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በውይይቱ ላይ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት አባል የሆኑት ታዋቂዋ ኢኮኖሚስት ዶክተር እሌኒ ገብረመድሕን ተሳትፈዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል ይኸው የዶክተር እሌኒ ተሳትፎ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በርካታ ነቀፌታ አዘል አስተያየቶችን አስተናግዷል፡፡ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ከተሰነዘሩ አስተያየቶች መካከል በምርጫ ሥልጣን ላይ የወጣ አካል ላይ የተደረገ ነው በሚል ተሳትፏውን ‹‹ክሕደት ነው›› ያሉም መኖራቸው ተስተውሏል፡፡

ከቀናት በፊት በተመሳሳይ ለገጣፎ አካባቢ የሚገኘው ቤቴ በጸጥታ ኃይሎች ተበርብሯል ማለታቸውን ተከትሎ መነጋሪያ ሆነው የነበሩት ዶክተር እሌኒ ገብረመድኅን፣ የእሑዱን ምስጢራዊ የተባለ ውይይት አስመልክቶ ስለ ተሳትፏቸው እና ተሳትፏቸውን ተከትሎ ስለተሰነዘሩባቸው ነቀፌታዎች እንዲሁም አስተያየት ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልማት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር እሌኒ በትዊተር ባሰራጩት ምላሽ፣ ፒስ ኤንድ ደቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል ተዘጋጅቷል ባሉት ውይይት ላይ ያደረጉት ተሳትፎ ሆነ ተብሎ ተዛብቷል ያሉ ሲሆን፣ በዙም ውይይቱ ላይ ያደረጉት ተሳትፎ እንደ አንድ ሰላም ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ያደረጉት እንጂ ከቀጣሪያቸው ጋር እንዲሁም ከሰሞኑ ቤታቸው ከመፈተሸ ጋር የሚገናኝ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዶክተር እሌኒ በዚህ ማስተባበያቸው በውይይቱ ላይ የተነሱ ጉዳዮችን አንዳቸውንም እንደማይቀበሉ ጠቅሰው፣ በምርጫ ሥልጣን የያዘውን የኢትዮጵያ መንግስት የማጣጣል ድርጊት እንደሚኮንኑ እንዲሁም ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ አካሄድ ለሚደረግ የመንግስት ለውጥ ድጋፍ እንደማይሰጡም ገልጸዋል፡፡

እሑድ እለት የተደረገውን ይህን የዙም ውይይት በተመለከተም ሆነ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት አባሏ ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን ያደረጉትን ተሳትፎ በተመለከተ መንግስት አቋሙን ይፋ አላደረገም፡፡

በውይይቱ ተሳትፎ ነቀፌታ ያስተናገዱት የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በመስራችነት የሚታወቁት ዶክተር እሌኒ ገብረመድኅን፣ የከፍተኛ ትምሕርታቸውን ዓለም አቀፍ ደረጃ ሥመ ጥር ከሆኑት ስታንፎርድ፣ በሚችጋን እና ኮርኔል ዩኒቨርሲዎች ያገኙ ሲሆን፣ የስዊዘርላንድ ዜግነት ወስደዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img