አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 16፣ 2014 ― በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኃላፊነት ከጎደላቸው ሽብር ፈጣሪ መረጃዎችን ከመልቀቅ እንዲቆጠብ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው እለት አስጠንቅቋል።
ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካ ኤምባሲ በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ ሽብር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል ማለቱን ተከትሎ ሽብር ፈጣሪ መግለጫዎችን ሲያሰራጭ መቆየቱን አንስተዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲን የኮነኑት ሚኒስትር ዲኤታው፣ በአንጻሩ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች ዜጎቻቸውን ለማውጣት ያደረጉት ሙከራ ስህተት መሆኑ ሲገባቸው ሐሳባቸውን እየቀየሩ ነው ሲል ተደምጠዋል።
አያይዘውም በዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ ፍጹም ስህተት መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርብ ጊዜያት አሜሪካውያን ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ የሚለቀው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ማክሰኞ ኅዳር 14 ባወጣው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ሊኖር ይችላል ሲል በኢትዮጵያ ለሚኖሩ አሜሪካዊያን ዜጎች ማስጠንቀቂያ ሰዶ ነበር።
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደኣ፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የሽብር ጥቃት ቢደርስ ፈጻሚው ‹‹ሆነ ብሎ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሠራጨ ነው›› ያሉት የአሜሪካ መንግስት መሆኑን ገልጸው ነበር።