Sunday, September 22, 2024
spot_img

ወደ ላሊበላ እና ኮምቦልቻ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የጠየቀ አንድም የዓለም አቀፍ ረጂ የለም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 14፣ 2014 ― የአማራ ክልል ከተሞች ወደሆኑት ላሊበላ እና ኮምቦልቻ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የጠየቀ አንድም የዓለም አቀፍ ተቋም አለመኖሩን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገልጧል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንዳሉት ከሆነ፣ መንግስት ወደ ላሊበላ እና ኮምቦልቻ አየር ማረፊያዎች የሰብዓዊ ድጋፍ በረራ ፍቃድ ቢሰጥም እስካሁን ድረስ ድጋፍ ለማድረስ የጠየቀ አንድም የዓለም አቀፍ ተቋም እንደሌለ አሳውቀዋል።

በአካባቢዎቹ ለአምስት ወራት ያህል ድጋፍ ያላገኙና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች አሉ ያሉት አቶ ምትኩ ካሳ፣ መንግሥት ሁኔታዎችን ሲያመቻች ገብተው ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረብ ግዴታ ያለባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደተግባራዊ እርምጃ አልገቡም ማለታቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ ያመለክታል፡፡

አያይዘውም በሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ከተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ባለፉት ወራት እርዳታ ሳይቀርብላቸው የቆዩ ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚገኙ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች ወደአካባቢዎቹ እርዳታ ጭነው ቢሄዱና ሰብአዊ ድጋፍ ቢያቀርቡ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መታደግ የሚቻልበት አማራጭ መኖሩንም አሳውቀዋል።

የዓለም አቀፍ ተቋማት ጦርነት እየተካሄደባቸው በማይገኙ ቦታዎች ላይ ገብተው ድጋፍ የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት አቶ ምትኩ የሚሠሩት ሥራ የሰብዓዊነት ዓላማ እስካለው ድረስ የራሳቸውን መለያ እና አርማ አድርገው ድጋፍ ለማድረግ ወደየስፍራዎቹ መግባት ይችላሉ ሲሉ ገልፀዋል።

አማራና አፋር ክልሎች ያለው የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች ድጋፍ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ የገለፁት አቶ ምትኩ፣ ‹‹ችግሩን ለመፍታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ከየተቋማቱ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት አድርገናል። በዚህ መነሻነት ለውጦች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል›› ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ድጋፍ አላደረሱባቸውም የተባሉት የላሊበላ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በሕወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መሆናቸው ይነገራል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img