Friday, November 22, 2024
spot_img

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መከላከያን በግንባር ሆኖ ለመምራት ሊዘምቱ መሆኑን አሳወቁ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 14 2014 ― ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መከላከያን በግንባር ሆኖ ለመምራት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትግል ሜዳ እንደሚዘምቱ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን ሲሉ ባሰፈሩት ማስታወሻ ላይ ‹‹ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው›› ብለዋል፡፡

ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ›› የሚል መልእክት ሰደዋል፡፡

የእኛ መዝመት የሚፈጥረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት በሙሉ ዐቅማቸው ሸፍነው ይሠራሉ ያሉ ሲሆን፣ በግንባር ያልተሰለፉ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ ዐቅማቸው እንደሚከውኑም ገልጸዋል፡፡

ድሮም ሆነ ዛሬ የእያንዳንዳችን ፍላጎት፣ የሁላችንም ሕይወት ከኢትዮጵያ በታች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እኛ ኖረን ኢትዮጵያ ከምትሞት እኛ ሞተን ኢትዮጵያ እንድትኖር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

አያይዘውም የሁላችንም የሆነች፣ ነጻነትና ፍትሕ የሰፈነባት፣ በገናናነቷና በነጻነቷ በዓለም አደባባይ የምትጠራ ሀገር እንድትኖረን ምኞታችን ነው በማለት፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ በመመኘት፤ ሀገራችን አንገቷ ቀና እንዲል በመፈለግ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዐቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል ሲሉ አስፈረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ፖለቲካችን ከመገዳደል ወደ መተጋገል እንዲቀየር ታግለናል። ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በሰው ሀገር የሚንከራተቱት ሁሉ እንዲገቡ ለማድረግ ሞክረናል። ካለፈው በጎውን ወስደን ጥፋቱን በይቅርታ ለማረም ተንቀሳቅሰናል። “በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር” ብለን አዲስ ምዕራፍ ከፍተናል። የመለያየትና የጥላቻን ግንብ አፍርሰን የመደመርና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ድልድይን ልንገነባ ቃል የገባነውን ወደ ተግባር ለመተርጎም ዐቅማችን የፈቀደውን አድርገናል።

በተጨማሪም ኢኮኖሚው እንዲያገግምና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ፤ የዳኝነት ሥርዓታችን እንዲሻሻል፣ የሰብአዊ መብት አያያዛችን እንዲስተካከል፤ የውጭ ግንኙነት መርሐችን ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ታግለናል። በዚህ መካከል እንደ ሰው በርትተናል። እንደ ሰውም ደክመናል። እንደሰው አልምተናል፣ እንደ ሰውም አጥፍተናል። በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በኢትዮጵያ ክብርና በኢትዮጵያ ታላቅነት ግን ለአፍታም አዘንብለን አናውቅም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስታወሻቸው፣ ጎልማሶች በዘዴና በብልሃት አካባቢያቸውን እየጠበቁ፣ አረጋውያን እናትና አባቶች በጸሎት እየተጉ፣ ሁሉም ሰው ተባብሮ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋግጣል። ከዚህ በኋላ በሩቁ ተቀምጠን ተቺና አራሚ የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። መደረግ ያለበትን እኛው ራሳችን እናድርገው። ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም የአሸናፊዎች ስም ነው፤ የነጻነት ምልክት ነው። አልጠራጠርም፣ የእኔ ትውልድ ለአሸናፊ ስሙና ለነጻነት ምልክቱ የሚጠበቅበትን ዋጋ ከፍሎ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በክብር መዝገብ ላይ በወርቅ ብዕር ያትማል ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውሳኔ የመጣው የሚመሩት የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትላንት መወያየቱን ተከትሎ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img