አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 13፣ 2014 ― በአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና እስራኤልን ጨምሮ በበርካታ የዓለም አገራት ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በመንግሥት ላይ የሚደረገውን ጫና በመቃወም ሰልፍ አካሄደዋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በተሳተፉበት በዚህ ሰልፍ ላይ ሰልፈኞቹ በአሁኑ ወቅት የምዕራብ አገራት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያደርጉታል ያሉትን ጫና ተቃውመው ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
በሰልፎቹ ላይ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ያደርጉታል የተባለውን ጫና ከመቃወም ባለፈ፣ ሲኤንኤንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተዛቡ መረጃዎችን በማቅረብ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የድጋፍ ሰልፉ ከተደረገባቸው ከተሞች መካከል፤ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ኒውዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ኦስቲን፣ ሂውስተን፣ ቶሮንቶ፣ ኦታዋ፣ ካልጋሪ፣ ዊኒፒግ እና ለንደን ይገኙበታል፡፡
ሰልፎቹን ተከትሎ በዛሬው እለት በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ ሰልፎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ያጋሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ተደምረው ለእውነት ለቆሙ ኢትዮጵያውያን እና የአፍሪካ ቀንድ ዳያስፖራዎች አድናቆቴን እገልጻለሁ›› በማለት በሰልፎቹ ላይ የተስተጋባውን ‹ኖ ሞር› የሚል መፈክር አስተጋብተዋል፡፡