አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 11፣ 2014 ― የኢፌዴሪ ትምሕርት ሚኒስቴር ባለፈው ሰሞን ትምህርት ማቋረጣቸውን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ዓለም አቀፍ ት/ቤቶች ወደ ማስተማር መመለሳቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አስታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታዋ ሰላማዊት ካሳ እንዳስታወቁት በትምህርት ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች ሳንፎርድ፣ ቤንግሃም ት/ቤት እና የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲ ወይም በተለምዶ አጠራሩ የአሜሪካ ት/ ቤት ናቸው።
ትምህርት ቤቶቹ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ወዲያው የፊት ለፊት የመማር ማስተማር ስራ እና በኦንላይን ከሀገር የወጡ መምህሮችን በመጠቀም ትምህርት መጀመራቸው ተገልጧል፡፡
ትምህር አቋርጠው የነበሩት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች በምክንያትነት ያስቀመጡት ወቅታዊውን የፀጥታ ሁኔታ ነበርለ፡፡ ሆኖም የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት እነዚህ ነገሮች በህብረተሰቡ ላይ መደናገር ለመፍጠር የተቀናጀ ሀሰተኛ መረጃ የመንዛትና ዜጎችን ፍርሃት ውስጥ ለመክተት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የሚያሳዩና የሕወሓት መጠቀሚያ መሆኑን በግልፅ የታየበት ነው ብሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ 26 ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል 24 ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ የሚገኙ ናቸው፡፡