Sunday, September 22, 2024
spot_img

ባህር ዳር የተጠለሉ ተፈናቃዮች ከተማ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከላቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 11 2014 በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ጦርነት ተፈናቅለው ባህር ዳር የተጠለሉ ተፈናቃዮች በከተማ አስተዳደሩ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከላቸውን ተከትሎ ወደ መጡበት አካባቢ እየተመለሱ መሆኑ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ተፈናቃዮች ነግረውኛል ብሎ አስነብቧል፡፡

በባህር ዳር ከተማ ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮች አቅም ያላቸው በከተማዋ በግላቸው ቤት ተከራይተው፣ አቅም የሌላቸው በከተማዋ በተዘጋጁ መጠለያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መታወጁን ተከትሎ፣ ተፈናቃዮቹ በከተማዋ በነፃነት መንቀሳቀስና ወጥቶ መግባት አለመቻላቸው ተገልጧል።

በተለይ ከዋግኽምራ ሰቆጣ ዞን የመጡ ተፈናቃዮች በባህር ዳር ከተማ ከተጠለሉ ወራት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ቀድሞ የነበረው ነፃነታቸው እና ይደረግላቸው የነበረው እንክብካቤ ወደ እንቅስቃሴ ገደብ መቀየሩ ያልጠበቁት ነገር እንደሆነባቸው መናገራቸው ተመላክቷል።

“ከተማ አስተዳደሩ ያሠማራቸው ሕግ አስከባሪዎች የባህር ዳር መታወቂያ የሌላቸውን ተፈናቃዮች ከመስመር ላይ አያፈሱ ሲያስሩ ነበር” ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ወጣት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ወጣቱ አያይዞም ቀደም ሲል ተከራይተው የሚኖሩ ተፈናቃዮችም ይሁኑ በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በተለይ ወጣቶች፣ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ እንደሚታሠሩ ገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ሕግ አስከባሪዎች ተፈናቃዮችን በከተማዋ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከላቸውን ተከትሎ የተደናገጡት ተፈናቃዮች፣ በተለይ መጀመሪያ ወደ ባህር ዳር የገቡ ተፈናቃዮች ከባለፈው ሳምነት ጀምሮ መኪና መንቀሳቀስ እስከሚችልበት ቦታ ድረስ በመኪና በመሔድ ቀሪውን መንገድ በእግራቸው ተጉዘው ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን ጋዜጣው አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ባህር ዳር ከተማ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎችት በተዘጋጁ መጠለያዎች መጀመሪያ ከገቡት ተፈናቀዮች በተጨማሪ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጦርነቱ ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችም ጭምር ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ በመጠለያው እንደሚገኙ ተገልጿል። አዲስ ወደ ከተማዋ ከገቡት ተፈናቃዮች በተጨማሪ ቀድመው ከገቡ ተፈናቃዮች ውስጥ ሴቶች እና ሕፃናት በመጠለያ ጣቢያዎቹ እንደሚገኙም ተሰምቷል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከተው የባህዳር ከተማ አስተዳደር ስለ ጉዳዩ የሰጠው መረጃ ስለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img