አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 8፣ 2014 ― የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር አሰፋ ፍስሐ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ረዳኢ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቢቢሲ ከተለያዩ ታማኝ ምንጮቼ አረጋግጫለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰር አሰፋ ፍስሐ በሕገ መንግሥት ትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሆናቸውን ያመለከተው የዜና ምንጩ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ረዳኢ ደግሞ በአሰሪ እና ሠራተኛ ሕግ ዘርፍ አንቱታን ያተረፉ ምሁር ናቸው ብሏል።
ሁለቱም መምህራን በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የተዘገበ ሲሆን፣ ከታሳሪዎቹ መካከል ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ረዳኢ ከቀናት በፊት ለአንድ ቀን ታስራው እንደተፈቱ እና የአሁኑ ሁለተኛ እስራቸው እንደሆነም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ዲን የሆኑት ብሩክ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ ‹‹እስካሁን የማውቀው ነገር የለም›› ማለታቸው ሲዘገብ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታም ታሰሩ በተባሉት ግለሰቦች ጉዳይ ዙሪያ መረጃ እንደሌላቸው እና አጣርተው መልስ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ብቻ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል በትላናትናው እለት ባወጣው መግለጫው አስታውቋል፡፡
በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው ከጥቅምት 23 ጀምሮ መሆኑ ይታወቃል፡፡