አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 8፣ 2014 ― ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ እንዲገደል ግድያ ቦታ አመቻችታለች ተብላ የተከሰሰችው ላምሮት ከማል በ5 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንድትወጣ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መስጠቱ ተሰምቷል፡፡
በዛሬው እለት የዋስትና ትእዛዙን የሠጠው የከፍተኛው ፍርድ ቤት 2ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡
ችሎቱ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ሕግ 113 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት የጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ላምሮት የተከሰሰችበት የሽብር ወንጀል አንቀጽን በማሻሻል በቸልተኝነት የሚፈጸም የወንጀል ህግ አንቀጽ 575 መሰረት እንድትከላከል በተሰጠ ውሳኔ መሰረት አንቀጹ ዋስትና አያስከለክም ሲል ነው ዋስትና የተፈቀደላት።
ፍርድ ቤት በዚህ አንቀጽ የመከላከያ ማስረጃዋን ለመመልከት ለኅዳር 23 እና 24፣ 2014ዓ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በድምጻዊው ግድያ ተጠርጥረው ከተያዙ አራት ሰዎች መካከል የሆነችው ግለሰቧ፣ ግድያውን በማመቻቸት ተጠረጥራ የነበረ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም በወንጀል ድርጊቱ ውስጥ ተሳትፎዋን የሚያረጋግጥ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ዐቃቤ ሕግ አለመቅረቡን በመግለጽ በነጻ እንድትለቀቅ ቢወስንም፣ ይግባኝ ተጠይቆባት ነበር፡፡