አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 7፣ 2014 ― የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ሰብዐዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ የገቡ 872 ተሽከርካሪዎችን ሕወሓት ለጦርነት እየተጠቀመባቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሰብኣዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የገቡት 1 ሺሕ 114 ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ያስታወሱት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ደሲሳ፣ ከነዚህ ውስጥ 872 የሚሆኑትን ሕወሓት ለጦርነት እየተጠቀመባቸው ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አያይዘውም መንግሥት ለትግራይ ሰብዓዊ ርዳታ እንዳይደርስ ሆን ብሎ ያደናቅፋል በሚል ከውጭ መንግሥታት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች የሚቀርበው ክስ መሠረት የሌለው እንደሆነም የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታው በሰጡት መግለጫው ገልጸዋል።
አሁንም በጦርነቱ እና በወረራው ለተጎዱም ሆነ ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግሥት የሚያቀርበው ሰብዓዊ ርዳታ መቀጠሉንም አክለው ጠቅሰዋል።
ሕወሃት ራሱ ያደረሰውን የሰብዓዊ ቀውስ በመንግሥት እንደሚያሳብብ የገለጹት አቶ ከበደ ዴሲሳ፣ ሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦቱ በአንድ አካባቢ ብቻ የሚያስፈልግ እና እየቀረበም እንዳልሆነ ተደርጎ በአንዳንድ የርዳታ ተቋማት ክስ እንደሚቀርብና ክሱ ተቀባይነት የሌለው ከእውነታው የራቀ በመሆኑ ችግሩ በአንድ አካባቢ ብቻ የተፈጠረ እና በመንግሥት የተፈጠረ አድርገው የሚያቀርቡት መሠረተ ቢስ መሆኑ እንዲታወቅ ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው የሕወሃት ቡድን የወረራቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ከፍተኛ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍል እንዳለ ዓለምም ሆነ ለኅብረተሰባችን ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት በበኩሉ በየትኛውም አካባቢ ለሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረስ እንደሚሠራም ነው ሚኒስትር ዲኤታው ያመለከቱት።