አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 7፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ከታወጀበት ጥቅምት 23፣ 2014 ጀምሮ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር በሺሕዎች እንደሚገመት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በከተማው የታሰሩ ሰዎችን ብዛት በሚመለከት የተሟላ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም ያለው ኢሰመኮ፣ በአንጻራዊነት የተሟላ መረጃ ያገኘው ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሆኑን በመጥቀስ፣ መረጃው በተሰጠበት ኅዳር 2፣ 2014 በክፍለ ከተማው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ 714 ሰዎች መታሰራቸውንና ከነዚህም ውስጥ 124ቱ ሴቶች እንደነበሩ ለማወቅ እንደተቻለ አመልክቷል፡፡
በሌሎችም ክፍለ ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ እስሮች ሲከናወኑ ስለነበርና በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሂደት አሁንም የቀጠለ በመሆኑ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው ይገመታል ብሏል።
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ የአዲስ ከተማ፣ የልደታ፣ የጉለሌ፣ የቦሌ እና የአራዳ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎች ከበላይ ትእዛዝ ካልመጣልን መረጃ አንሰጥም፣ እስረኛም መጎብኘት አትችሉም በማለታቸው ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት እንዳይወጣ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
ኢሰመኮ የተወሰኑ ሰዎች በሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት መረጃ መሰረት የሚታሰሩ ናቸው ያለ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ግን ከህብረተሰቡ ተገኘ በተባለ ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉና ከመካከላቸው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች ብዛት ከፍተኛ መሆኑን ለማወቅ መቻሉን ጠቁሟል፡፡
በዚህ ረገድ ብሔር ተኮር እስር ስለመከናወኑ ተጠይቀው ለኮሚሽኑ ምላሽ የሰጡት የሕግ አስከባሪ አካላት ‹‹ሰዎች የሚያዙት በብሔራቸው ምክንያት ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ተጠርጥረው እንደሆነና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሁለቱም ድርጅቶች ብሔር ተኮር ድርጅቶች ከመሆናቸው አኳያ የሚያዙ ሰዎች የአንድ ብሔር ሊመስሉ እንደሚችሉ›› ተናግረዋል ሲል በመግለጫው አስፍሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ በድሬዳዋ ከተማ ደግሞ እስከ 300 የሚሆኑ ሰዎች ታስረዋል ብሏል።
ኢሰመኮ በመግለጫው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራሉ ተብለው ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠሩ ሰዎችን ይዞ የማቆየት ሥልጣን ለሕግ አስከባሪ አካላት መስጠቱን እና የተባሉት ቡድኖች ብሔር ተኮር ድርጅቶች መሆናቸውን እንደሚገነዘብ በማስፈር፣ ይሁንና በጥቆማ ላይ የተመሰረቱ እስሮችን በተመለከተ የጥቆማዎቹ መነሻ የሰዎቹ የብሔር ማንነት አለመሆኑን ለማረጋገጥ እና ምክንያታዊ ጥርጣሬ ስለመኖሩ ለማጣራት በቂ ጥረት እየተደረገ አይደለም ብሏል። በተጨማሪም በአንዳንድ ጣቢያዎች ከአዋጁ ጋር በተያያዘ የተያዙ ሰዎች የትግራይ ተወላጅ አለመሆናቸውን በማሳየት ከእስር ሲፈቱ የኢሰመኮ ባለሞያዎች መመልክታቸውን ገልጧል፡፡
ኮሚሽኑ አደረግኩት ባለው ክትትል ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መተግበር ባለበት መንገድ በተለይም ‹‹የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ መሆን›› የሚሉትን የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ አለመተግበሩን ተመልክቻለሁ ነው ያለው፡፡
በመሆኑም ሕግ አስከባሪ አካላት በጥቆማ ብቻ የተያዙ ሰዎችን ጉዳይ በመመልከት አዋጁ በሚጠይቀው መሰረት ምክንያታዊ ጥርጣሬ መኖሩን የሚያረጋገጥ መረጃ ያልተገኘባቸውን ሰዎች፣ እንዲሁም በተለይም በቁጥጥር ስር የዋሉ አረጋውያን፣ የሚያጠቡ እናቶች እና የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቁ ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም እስር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መንፈስ በመረዳት በተመጣጣኝነት፣ በጥብቅ አስፈላጊነታቸው እና ከመድልዎ ነፃ በሆነ መልኩ እንዲከናወን፣ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉ፣ በተለይም የሚያዙ ሰዎች ሁሉ የታሰሩት በምክንያታዊ ጥርጣሬ መሰረት ብቻ መሆኑን የሕግ አስከባሪ አካላት በጥብቅ እንዲያረጋግጡ ብሏል፡፡
ከታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ አያያዝ ጋር በተገናኘ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ በተለይም የጤና፣ የመጸዳጃ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲመቻቹ አሳስቧል፡፡ አያይዞም ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወቅትን ጨምሮ በማናቸውም ጊዜ ሰብአዊ መብቶችን የሚከታተል መሆኑን በመገንዘብ እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለኮሚሽኑ የክትትል ተግባራት ትብብር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው በመረዳት ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉለት ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት በተለይ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ያላቸው እስሮች መበራከታቸው አሳስቦኛል ብሏል፡፡
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል በአዲስ አበባ፣ በጎንድር፣ በባሕር ዳር እና በሌሎች ስፍራዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ፖሊስ ፍተሻ እያደረገ እና በርካታ ሰዎችን እያሰረ ነው ብለዋል።
ቃል አቀባይዋ ትላናት ማክሰኞ ጄኔቭ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ያሉት አብዛኞቹ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸውም አልያም ደጋፊ ናቸው የሚባሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው ብለዋል።