Sunday, September 22, 2024
spot_img

በሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረ ብረሃን ውጭ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ዞኑ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 6፣ 2014 ― በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረ ብርሃን ከተማ ውጪ በሚገኙ የገጠር ወረዳዎች ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን የዞኑ የአደጋ ሥጋት እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አበባው መሰለ ገልጸዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በሸዋሮቢት፣ መሃል ሜዳ፣ ጫጫ፣ ጣርማ በር እና መርሃ-ቤቴ፣ በአጠቃላይ በአስራ አንድ የገጠር ወረዳዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በተዘጋጁ የመጠለያ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም በከተማው ነዋሪዎች ቤት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

በዚህም ተፈናቃዮቹ ደብረ ብርሃን ከሚገኘው ከዋናው ማስተባበሪያ ባላቸው ርቀት እና ቁጥራቸውም በውል ባለመታወቁ ከደብረ ብርሃን ወደ ወረዳዎች የሚላከውን የሰብዓዊ ዕርዳታ በአግባቡ ማድረስ መቸገሩን ነው የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ የገለጹት።

ከሰሞኑ ሰሜን ሸዋ ከሚገኙ ወረዳዎች ከማጀቴ፣ ኤፍራታና ግድም፣ እንዲሁም ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ እየተፈናቀለ ወደ ደብረ ብርሃንና ሌሎች ወረዳዎች እየገባ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቁጥሩ በቀጣይም ሊጨምር ስለሚችል የዕርዳታ ቁሳቁሶች ዕጥረት ሊያጋጥም ይችላል ሲሉ ኃላፊው ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በአጣዬና አካባቢው ለነበረው ሥጋት ለመጠባበቂያነት የተያዘውን የዕርዳታ ቁሳቁስ ነው እያቀረብን ያለነው ያሉት ኃላፊው፣ ወደፊት ኹሉም የሚመለከታቸው አካላት እርብርብ ካላደረጉ በተፈናቃዮች ላይ ከባድ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ነው የተናገሩት።

ድጋፍ እየተደረገ ያለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙት ተፈናቃዮች ሲሆን፣ ከመጠለያ ውጪ የሚገኙትን ቤት ለቤት ምዝገባ እየተካሄደ በመሆኑ፣ በቀጣይ ኹሉም ወደ ካምፕ እንዲሰባሰቡ ሲደረግ ከፍተኛ የዕርዳታ ዕጥረት ሊከሰት ይችላል ብለዋል።

በዚህ ወቅት ደብረ ብርሃን ከተማ ያሉትን ጨምሮ ወደ 220 ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች በዞኑ አስራ ኹለት ወረዳዎች መኖራቸውንም ጨምረው አንስተዋል። በደብረ ብርሃን ከተማ 145 ሺሕ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ሦስት ሺሕ 541 የሚሆኑ አባዎራዎች ከነ ቤተሰቦቻቸው 17 ሺሕ 705 ሆነው በስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙም አመላክተዋል።

ቀሪዎቹ ደግሞ ሆቴል ወይም ቤት ተከራይተው ይኖራሉ ያሉት ኃላፊው፣ አንዳንድ የከተማ ነዋሪዎችም ከ25 እስከ 40 የሚደርሱ ተፈናቃዮችን በየቤታቸው አስጠልለው እንደሚገኙ ም አንስተዋል፡፡

በዞኑ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ የመጣው ከደሴ ከተማና ከሰሜን ወሎ ሲሆን፣ በመቀጠል ከደቡብ ወሎ እና ከዋግ ኽምራ መሆኑ ተነግሯል። ከተናቃዮች ውስጥ ለሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና ነፍሰጡር ሴቶች ለብቻ ማረፊያ ተዘጋጅቶ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት ያለው ዋነኛ ዕጥረት የመኝታ ፍራሽ መሆኑ ተነግሯል።

እንዲሁም በርካታ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ስለሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ትምህርት መጀመር ስላለባቸው፣ ተፈናቃዮች ትምህርት ቤቶችን ለቀው ሲወጡ የመጠለያ ዕጥረት እንደሚያጋጥም ተጠቁሟል።

አሁን ላይ በማኅበረሰቡና ግብረሰናይ ድርጅቶች በኩል ለተፈናቃዮች ዕርዳታ እየደረሰ እንዳለ በመግለጽ፣ ኃላፊው ተፈናቃዮች የተጎዱ ሰዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ ብዙዎች አረጋውያን፣ እመጫቶችና እርጎዞች በመሆናቸው እነዚህን ወገኖቻችን ለመርዳት ኹሉም የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img