Thursday, November 21, 2024
spot_img

ወደ አማራ ክልል በተዛመተው ጦርነት እስከ ነሐሴ መገባደጃ ድረስ ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ይፋ አደረገ

  • በሕወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩት ከተሞች የሚኖሩ የአዕምሮ ህሙማን ‹‹ሰላይ ናችሁ›› በሚል ምክንያት እና በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው በሕወሓት ታጣቂዎች መገደላቸውም በሪፖርቱ ተካቷል

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 4 2014 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሐምሌ ወር 2013 ጀምሮ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በሕወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል። 

ከሰኔ 21 ቀን እስከ ነሐሴ 22፣ 2013 ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው ይህ ሪፖርት እስከ ነሐሴ 30፣ 2013 ድረስ የተካሄደ ምርመራ ውጤት ሲሆን፣ የምርመራ ቡድኑ 128 ቃለመጠይቆችን፣ ከተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሲቪል እና የፀጥታ አካላት፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት፣ ከተራድዖ ድርጅቶች  ጨምሮ 21 የቡድን ውይይቶችን ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ያደረገው ምርመራ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማ፣ ፋርጣ ወረዳ፣ ጉና በጌምድር ወረዳ፣ ነፋስ መውጫ ከተማ እና የላይ ጋይንት ወረዳ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ሃራ፣ ወልዲያ፣ መርሳ፣ ሃብሩ፣ ኡርጌሳ እና ቆቦ እና በደቡባዊ ትግራይ አላማጣ ከተሞችን የሚያካትት ነው፡፡

የምርመራ ቡድኑ ሰሜን ወሎ ዞን እና ደቡባዊ ትግራይ የሚገኙ ቦታዎችን በጦርነቱ ምክንያት መድረስ ባለመቻሉ ለምርመራ ሥራው የሚሆነውን መረጃ ያገኘው ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና ሃይቅ ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ከሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ፣ ወልዲያ እና አካባቢው እንዲሁም ከደቡባዊ ትግራይ መሆኒ፣ ማይጨው እና አላማጣ አካባቢ የመጡ ተፈናቃዮችን በማነጋገር መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ እንዳመላከተው ምርመራው ባተኮረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ በምርመራዬ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ በተለይ የሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን፣ ሰፊ የንብረት ዘረፋ እንዲሁም ውድመት ሆን ብለው መፈፀማቸውን አረጋግጫለሁ ነው ያለው፡፡

 

የሕወሓት ታጣቂዎች በየአካባቢው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን የገደሉት የገዥው ፓርቲ ወይም የመንግስት ደጋፊ ናችሁ፣ መንገድ ወይም ቦታ አላሳያችሁንም፣ የቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን አስጠግታችኋል ወይም ደግፋችኋል፣ ንብረት አምጡ በሚሉ እና ለጊዜው ባልታወቁ ሌሎች ሁኔታዎች ወይም ምክንያቶች ጭምር ነው፡፡ በሕወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩት ከተሞች የሚኖሩ የአዕምሮ ህሙማን ‹‹ሰላይ ናችሁ›› በሚል ምክንያት እና በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው በሕወሓት ታጣቂዎች መገደላቸውም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት የሕወሓት ታጣቂዎች ሲቪል ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ ሆነው የሚፈፅሙበትን ጥቃት ለመከላከል እና ለማጥቃት ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀሙ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና አካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ንብረትም እንዲወድም ሆኗል ብሏል፡፡

 

በጦርነቱ በሁለቱም ወገን በኩል የተተኮሱ የተለያዩ ከባድ መሳሪዎች በሲቪል ሰዎች ሕይወት እና አካል ጉዳት ጨምሮ በሲቪል መሰረተ ልማቶች፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆስፒታሎች፣ በእምነት ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው መረጋገጡም ነው የተገለጸው፡፡

 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ‹‹በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ግኝቶች በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው›› ብለዋል። አያይዘውም ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ሲቪል ሰዎችን ከጦርነቱ ሰለባነት የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲያከብሩና የድርጊቶቹን ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

ኮሚሽኑ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተጨማሪ አካባቢዎች ቀጣይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የሆነ የጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊ የሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ መቅረቡን ጨምሮ በዚሁ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img