Monday, October 7, 2024
spot_img

ቀደም ብለው ከወጡ ሕጎች እና መመሪዎች ውጭ ሲሠሩ በሚገኙ ባንኮች ላይ ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ ተላለፈ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 2፣ 2014 ― በአገሪቱ ቀደም ብለው ከወጡ ሕጎች እና መመሪዎች ውጭ ሲሠሩ በሚገኙ ባንኮች ላይ ጥብቅ ርምጃ እንዲወስድ ለብሔራዊ ባንክ ትእዛዝ ያስተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ነው፡፡  

ይህንኑ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው እዙ፣ ትእዛዙን ለማስተላለፍ መነሻ የሆነው ‹‹ሕገ ወጥ›› ያላቸው ግለሰቦች ‹‹ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው ደንቦችና የአፈጻጸም መመሪያዎች እንዲሁም ከባንኮች ሕጋዊ አሠራር ውጭ፣ በተጭበረበረ መንገድ የገንዘብ ዝውውር እያካሄዱ መሆኑ›› ስለተደረሰበት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ቀደም ብለው ከወጡ ሕጎች እና መመሪዎች ውጭ ሲሠሩ በሚገኙት ባንኮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሕግ አስፈጻሚ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥብቅ ርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ ከማስተላለፉ በተጨማሪ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማንኛውም የተጭበረበረ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ሰነድ ይዘው በተገኙ ላይ ከወትሮው በተለየ ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድ ብሏል፡፡

በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ በዚሁ መግለጫው የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማስፈጸም ባለፉት ቀናት ‹‹አኩሪ ውጤቶችን›› ማስመዝገቡን ያመለከተ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሎች ለሕዝቡ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑትን ለመመንጠር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲያግዛቸው ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራይን ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ ከትላንት ኅዳር 1፣ 2014 ጀምሮ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ በአቅራቢያው በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ እንዲያስመዘገብ አዟል፡፡

አያይዞም የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ በማድረግ ሕገ ወጦችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን፣ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችም እንደተያዙ ገልጧል፡፡ ነገር ግን ‹‹ይህ ያስደነገጠው›› ጠላት ያለው አካል፣ ‹‹የጸጥታ አካላትን መልካም ስም ለማጥፋት፣ ለማሸማቀቅና ሥራቸውን በሙሉ አቅም እንዳይሠሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ›› እንደሚገኝ አሳውቋል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ አጋጣሚ ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት የጸጥታ አካላት መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ያለው እዙ፣ በእነዚህ አካላት ላይ በጠራ መረጃ ላይ በመመሥረት የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ መሰጠቱንም አክሏል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጥቅምት 23፣ 2014 በመላው ኢትዮጵያ የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የተቋቋመ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img