አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 30፣ 2014 ― የአዲስ አበባ ፖሊስ በከተማው ጥበቃ ከተጀመረ በኃላ የተለያዩ የጦር መሪያዎች በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች፣ በየጥሻው እና በየመንገድ ዳር ተጥሎ እየተገኘ መሆኑን አስታውቋል።
ፖሊስ በየ ገንዳው እና ጥሻው እየተገኙ ነው ያላቸው የጦር መሳሪያዎች የእጅ ቦንብ ጨምሮ መሆኑን የዘገበው ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ነው።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንኑ ተረድቶ በእነዚህ አካባቢዎች ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና ጥቆማም እንዲሰጥ አሳስቧል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ፖሊስ ህብረተሰቡ በቡድን በቡድን እየሆነ በየአካባቢው ጠንካራ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን በመጠቆም፣ በዚህም በርካታ ውጤት መገኘቱን አሳውቋል።
ፖሊስ ለከተማው የፀጥታ ስጋት ናቸው የተባሉ፣ ሀገርን ለማፍረስ ለተሰለፉ ኃይሎች በተለያዩ መልኩ ሲደግፉ የነበሩ፣ ስልጠናና ስምሪት ተሰጥቷቸው በከተማው የተሰገሰጉትን እየለየን እየያዝን ነው እንዳለውም ራድዮ ጣቢያው ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከቀናት በፊት በከተማው ውስጥ ማንኛውም የጦር መሳሪያ ያለው ግለሰብ እንዲያስመዘግብ መመሪያ ማስተላለፉ አይዘነጋም።