Saturday, November 23, 2024
spot_img

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እስራኤል ወንጀለኞችን ከስደተኞች ጋር ቀላቅላ ከኢትዮጵያ ወስዳለች በሚል በመሪዋ ላይ ወቀሳ ማቅረባቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 30 2014 – የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በእስራኤል አቻቸው ናፍታሊ ቤኔት ላይ አገራቸው ወንጀለኞችን ከስደተኞች ጋር ቀላቅላ ከኢትዮጵያ እንዲሄዱ አድርጋለች በሚል ወቀሳ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡

ቻናል 13 የተባለው የእስራኤል ቴሌቪዥን እንደዘገበው፣ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ሥሙ ካልተጠቀሰ የጦርነቱ አካባቢ ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ የተደረገበት የእስራኤል ደህንነት ተቋማትን ያሳተፈ ዘመቻ ተካሄዷል፡፡

ይህ ዘመቻ ኢላማ ያደረገው የደህንነት ስጋት ገጥሟቸዋል የተባሉ 77 ኢትዮጵያውያንን በምሥጢር ወደ እስራኤል መውሰድ እንደነበር ተገልጧል፡፡ እንደ ዘገባው በዚሁ እስራኤል ባካሄደችው ዘመቻ ወደ እስራኤል ከሄዱት 77 ሰዎች መካከል 3 ወይም 4 ሰዎች አገር ውስጥ በተካሄደ ጭፍጨፋ ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው የሚፈለጉ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለእስራኤል አቻቸው ነግረዋቸዋል፡፡

ጉዳዩ ወደ አደባባይ የወጣው በተደረገው ማጣራት በምሥጢር ወደ እስራኤል የተወሰዱት 77 ግለሰቦች የአይሁድ ዝርያ የሌለባቸው መሆኑን ተከትሎ በመንግስት ውስጥ በተፈጠረ ውዝግብ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡ ውዝግቡ የተፈጠረው የእስራኤል የአገር ውስጥ ቢሮ የሰዎቹን ማንነት አጣርቶ ባወጣው ሪፖርት ላይ ጉዳዩ የሚመለከተው መስሪያ ቤት ሰዎቹን ወደ እስራኤል ለማምጣት የወሰነበት መንግድ እውነተኛ ማጣራት የተደረገበት አልነበረም በማለቱ ነው፡፡

 

ነገር ግን የአይሁድ ዝርያ ሳይኖርባቸው ወደ አገሪቱ በደህንነት ሰዎች ታግዘው የተወሰዱ በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን ቀጣይ እጣ ፋንታ በተመለከተ ከሁለት አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የስልክ ንግግር በኋላ የተወሰነ ነገር ስለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img