Sunday, September 22, 2024
spot_img

በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ የሕወሓት ተዋጊዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለሱ አሳሰቡ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 30፣ 2014 – በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የሕወሓት ተዋጊዎች ጥቃታቸውን ወደ አዲስ አበባ እንዳያሰፉ እና አሁን ከያዟቸው አካባቢዎች በመልቀቅ ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለሱ አሳስበዋል፡፡  

የጸጥታው ምክር ቤት በትላንትናው እለት ለ12ኛ ጊዜ ባደረገው ስብሰባ ላይ የተናሩት ሊንዳ፣ አንድ ዓመት ባስቆጠረው ጦርነት ወቅት ለረዥም ጊዜ በዝምታ ቆይተናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት መጠነ ሰፊ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን የተናገሩት ተወካዩዋ፣ ይህም መድፈርን እንደ የጦርነት መሳሪያ መጠቀምን ያጠቃለለ ነው ብለዋል። በዚህ ጦርነት ሁሉም ኃይሎች ጥፋተኞች ናቸው፤ ጥፋት የለሌለበት የለም ያሉ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ለአንድ ወገን ያዳላል በሚል የሚቀርበበት ክስ አግባብ እንዳልሆነም አያይዘው አጣጥለውታል፡፡

ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በዚሁ ንግግራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎችን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ሕጎችን እንዲያከብር የጠየቁ ሲሆን፣ ሰላምን ሊያመጡ የሚችሉት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በምክር ቤቱ ስብሰባ ኢትዮጵያን ወክለው የቀረቡት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፣ መንግሥት ባለፈው አንድ ዓመት ከሕወሓት የተቃጣበትን ወታደራዊ አደጋ መመከቱን ተናግረዋል። አክለውም መንግሥት ምግብን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅሳቁሶችን በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመተባበር ሲያቀርብ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ‹‹ይህ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል›› ሲሉ የተደመጡት አምባሳደሩ፣ ለችግሩ በዋናነት ‹‹የወንጀል ቡድን›› ነው ያሉትን ሕወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ ያስፈልገው የነበረውን አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እንዳያገኝ እንዳደረገውም ነው ያመለከቱት፡፡

በሌላ በኩል ‹‹መንግሥት ወደ ትግራይ ምግብ እና መድኃኒት ጭኖ የላካቸው ተሽከርካሪዎች የጦር መሳሪያዎችን እና ወጣት ተዋጊዎችን እያጓጓዙ ነው›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ወጣቶቹ ከወንድሞቻቸው ጋር አንድም የሕዝብ ጥቅም በሌለበት ለጥቂት ስግብግብ ሰዎች ሲባል እንዲዋጉ ተገደዋል›› ብለዋል፡፡

‹‹ለፖለቲካዊ ውይይት የሚደረጉ ጥሪዎችን እናከብራለን›› ያሉት አምባሳደር ታዬ፣ የምዕራባዊያኑ መገናኛ ብዙኃን ብሎም የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞች እንዲሁም አመራሮች ለሕወሓት በይፋ ድጋፋቸውን ሰጥዋል የሚል ክስ አሰምተዋል።

በዚሁ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ቻይናን የወከሉት ዣንግ ጁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የብሔርና ሌሎች ምክንያቶች ጥምር ውጤት መሆኑን ጠቁመው፣ መፍትሔ የሚገኘው በአገር ውስጥ ብቻ መሆኑን አስምረውበታል።

በአህጉሪቱ ያሉ አገራትና ድርጅቶች ፖለቲካዊ እልባት ለማምጣት ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉም የአገራቸውን አቋም አስረድተዋል።

የቻይናው ተወካይ፣ አባል አገራቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና አመራር በማክበር ኢትዮጵያ የሰብአዊ አቅሟን እንድታሻሽል እና የሚሰጠው እርዳታም ሊጨምር ይገባል ብሏል።

ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ በቅርቡ በመንግሥት የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እንደ ሰበብ በመጠቀም የሰብዓዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ ሕጎች ችላ መባል እንደሌለባቸው አስጠንቅቀዋል።

በትላንትናው እለት የተሰበሰበው የጸጥታው ምክር ቤት፣ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተውና አንድ ዓመት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማርገብ የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ላለው የሰላም ተነሳሽነት ድጋፍ ሰጥቷል።

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img