Friday, November 22, 2024
spot_img

የመንግሥት ሹሙ በዋሺንግተን ጥምረት የፈጠረውን የፖለቲካ ቡድን ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ መሠረት የሌለው ደካማ ስብስብ ነው ሲሉ አጣጣሉት

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 27፣ 2014 ― ዘጠኝ የፖለቲካ ቡድኖች ‹የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት› በሚል በሥልጣን ላይ ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እንተካለን በሚል በአሜሪካ ዋሺንግተን ጥምረት መመስረታቸውን ትላንት ምሽት አስታውቀዋል።

ጥምረቱን አስመልክቶ ለቢቢሲ ኒውስ አወር የተናገሩት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ፣ ጥምረቱ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ መሰረት የሌለው ደካማ ስብስብ ነው ሲል አጣጥለውታል።

በጥምረቱ ውስጥ ትብብር ለመፈጠር ከፈረሙት መካከል ሕወሓት፣ የኦሮሞ ነጻነት ጦር፣ የሲዳማ ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይገኙበታል።

ይህ ጥምረት በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የመመሥረት ዓላማ እንዳለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር የተባለው ቡድን ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ እንደነገረው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጥምረት መመስረት አለመደነቃቸውን ያመለከቱት የመንግስት ሹሙ፣ ስብስቡን ‹‹ደካማ የፖለቲካ ኃይል ነው›› በማለት ገልጸውታል።

በሥነ ሥርዐቱ ላይ የጥምረቱን አላማ በተመለከተ የተናገሩት የሕወሓት ኃይሎችን በመወከል የተገኙት አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ፣ አላማቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን በኃይል አልያም በድርድር በማስወገድ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ግን ‹‹እነዚህ አማጺያን ቡድኖች መሠረት የላቸውም። ምንም አይነት ማኅበራዊ መሠረት የላቸውም፤ ምንም ለውጥ ሳያመጡ ላለፉት 40 ዓመታት እዚያው የቆዩ ናቸው›› ብለዋቸዋል፡፡ አቶ ከበደ ዴሲሳ ጨምረውም ‹‹በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት በሚያስፈልግበት ጊዜ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች መንግሥት ተዳክሟል፣ ሥልጣን ላይ መቆየት አይችልም ብለው ሲያስቡ ተሰባስበው ትብብር ይፈጥራሉ›› በማለት ሁኔታው የተለመደ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘጠኝ የፖለቲካ ቡድኖች ‹የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት ኃይሎች› በሚል በአሜሪካ ዋሺንግተን የፈጠሩትን ጥምረት ሬውተርስን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን ሰጥተውታል፡፡

አንድ ዓመት የዘለቀው በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት በቅርብ ቀናት የሕወሓት ኃይሎች የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን አልፈናል ማለታቸውን ተከትሎ ተባብሶ መቀጠሉን የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img