Saturday, November 23, 2024
spot_img

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስነው ድንበሯን ዘጋች

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 25፣ 2014 ― ጎረቤት አገር ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስነው ድንበሯን መዝጋቷን የአገሩ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲቲዝን ዘግቧል፡፡ ኬንያ ድንበሯን የዘጋችው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ከሚገኘው ጦርነት ጋር በተገናኘ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

የኬንያ ድንበር የመዝጋት ዜና የመጣው በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ መታወጁን ተከትሎ ነው፡፡ ከሰሞኑ በበረታው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ኃይሎች ጦርነት የሕወሓት ኃይሎች የአማራ ክልል ከተሞች የሆኑት ደሴ እና ኮምቦልቻን አልፈናል የሚል መረጃዎችን አሰራጭተዋል፡፡ ሆኖም ከመንግሥት በኩል ከተሞቹን አልፈናል ማለታቸውን በተመለከተ በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበሯን የዘጋችው ኬንያ፣ በድንበር የሚካሄዱ ዝውውሮችን መግታትን ታሳቢ ማድረጓን ማሳወቋ ነው የተገለጸው፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ተፋላሚ አካላት በአስቸኳይ የተኩስ አቁም አድርገው ለንግግር እንዲቀመጡ ጠይቀዋል፡፡

ኡሁሩ በጽሕፈት ቤታቸው በኩል ባሰራጩት ደብዳቤ፣ ጦርነቱ መፍትሔ እንዲበጅለት በግላቸው ከአፍሪካ እንዲሁም አሜሪካን ጨምሮ ከኃያላን አገራት መሪዎች ጋር መምከራቸውን አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን ያመለከቱት የኬንያው ፕሬዝዳንት፣ በተፋላሚ አካላት መካከል ንግግር ባለመኖሩ ጦርነቱ ቀጥሎ፣ የሚያስከተለውን ሰቆቃም መግታት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

ኬንያም ሆነ መላው አፍሪካ የኢትዮጵያን ሰላም መሆን ይፈልጋሉ ያሉት ኬንያታ፣ ለሰላም የሚደረገው ጉዞ መጀመሪያ ቀን ዛሬ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ኬንያ ባለፈው የፈረንጆቹ ወር ጥቅምት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታውን ምክር ቤት መምራቷ ይታወቃል፡፡ ፕሬዝዳንትዋ ኡሁሩ ኬንያታም በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋባዥነት በዚያው ወር ዋይት ሐውስ ተጋብዘው ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተገናኝተዋል፡፡

ኡሁሩን የጋበዙት ባይደን፣ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ የጦር መሳሪያ እና የአጎዋ እድልን በተመለከተ ሁለት እግዶችን በተያዘው ሳምንት አስተላልፈዋል፡፡

በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት በትላናትናው እለት አንድ ዓመት ደፍኗል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img