Sunday, September 22, 2024
spot_img

ጀነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ከመንግሥት ጋር ድርድር ለማድረግ ጊዜው አልፏል አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 23፣ 2014 ― ከመንግሥት ጋር እየተፋለሙ የሚገኙት የሕወሓት ኃይሎችን ይመራሉ ተብሎ የሚነገርላቸው ጀነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለድርድር ጊዜው አልፏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከክልሉ ቴሌቪዥን ጋር ረዥም ቆይታ ያደረጉት ጀነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ፣ ድርድር የማይኖረው ‹‹ጦርነቱ እያለቀ ስለሆነ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ሌሎች አማራጮች አሉ ያሉት ጻድቃን፣ ‹‹የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በመሰባሰብ ተወያይተው የሚያቆሙት የሽግግር መንግስት›› እንደሚያስፈልግና በዝርዝር ባያብራሩትም፣ በዚህ ረገድ እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ጥቅሰዋል።

አገሪቱ ወደ ሰላም የምትሸጋገርበት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ያስታወሱት ጀነራል ጻድቃን፣ የትግራይን እድል የሚወስነው ግን ራሱ የትግራይ ሕዝብ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሄ መብት ሕገ-መንግስታዊ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

አሁን ያለውን የፌዴራል መንግሥት ‹‹አገሪቱን ለማጥፋት ወንጀል የፈጸመ ነው» በሚል የወነጀሉት ጻድቃን፣ «አገሪቱን ልትወጣው የማትችልበት አዘቅት ውስጥ የከተተ በመሆኑ ተጠያቂ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

ጀነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ከዚህ ባሻገር ከጦርነቱ ቀድሞ የነበሩ ጊዜያትንም በቃለ ምልልሳቸው አንስተዋል፡፡ በዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በግላቸው ለሦስት ጊዜያት እንደተገናኙ የተናገሩ ሲሆን፣ ከምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ከኢፌዴሪ መከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ ጋርም ተገናኝተው ጦርነቱን ለማስቀረት መምከራቸውን አውስተዋል።

ከትግራይ ህዝብ ጋር እየተጣሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ይህ በሰላም እንዲፈታ እንደሚያግዟቸው መናገራቸውን አስታውሰው ጠ/ሚኒስትሩ ግን «ብርና ኃይል የማይፈታው ችግር የለም» በሚል ሥጋታቸውን እንዳጣጣሉባቸው ጀነራል ጻድቃን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኤርትራን መንግስት እና ፕሬዝዳንቱ ኢሳይያስ አፈወርቂን በተመለተከተም ያነሱ ሲሆን፣ ኢሳይያስን «ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለግኩ ልሁን ሲል ተው ስለተባለ ብቻ ፖሊሲ ቀርፆ ሀገሩን መለወጥ ሲችል» ለሁሉም ውድቀቱ ሕወሓትን ተጠያቂ ሲያደርግ መቆየቱንና ለበቀል መነሳሳቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የጸጥታና ዋነኛ የኢኮኖሚ ተቋማት በሻእቢያ ሰዎች መያዙን በእርግጠኝነት እንደሚያውቁ የተናገሩት ጀነራል ጻድቃን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከ27 በላይ በመንግስት የሚታወቁ የውጪ የምንዛሬ ቢሮዎች ኤርትራውያን እንደተቆጣጠሩትና፣ የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ገንዘብ በገፍ ወደ ኤርትራ እንደሚጓዝ ተናግረዋል።

የጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ቃለ ምልልስ የመጣው ከሰሞኑ የሕወሓት ኃይሎች የአማራ ክልል ከተሞች የሆኑትን ደሴ እና ኮምቦልቻን መያዛቸውን መነገሩን ተከትሎ ነው፡፡

ከሰሞኑ ያለውን ጦርነት በተመለከተ በትላንትናው እለት ለሚኒስትሮች እና ለሚኒስቴር ዴኤታዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው በወሎ ግንባር «የውጪ ዜጎች» ከሕወሓት ወግነው በጦርነቱ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳታዎቹ «የኢትዮጵያ ዝርያ የሌላቸው ነጮች እና ጥቁሮች›› መሆናቸውን ከመጥቀስ በዘለለ ማብራሪያ አልሰጡም፡፡

በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተላለፈው በዚህ ንግግር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ጦርነቱን አሁንም መንግሥት እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሕወሓትን በተመለከተም ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ «ምንም ጦርነት ሳናደርግ ይህን ሃይል ብንቀበለው፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትናንትናውን ሕወሓት ሳይሆን የዘመነውን ሕወሓት ለመሸከም ጫንቃዋ አይችልም» ብለዋል፡፡

አክለውም «አሁን ማሸነፍ፣ መሸነፍ ሳይሆን እኩይ አላማው የሚሳካበትም ጭላንጭል መንገድ የለም፣ የኢትዮጵያ አውድ ተቀይሯል። ከተቀየረው የኢትዮጵያ አውድ ጋር መቀየር የሚችል ኃይል አይደለም» ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አሁን እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት አላማ «በትጥቅ ኃይል መንግሥት የመፍጠር ፍላጎት ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው ማድረግ ነው» ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት በነገው እለት አንድ ዓመት ይደፍናል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img