Friday, November 22, 2024
spot_img

በሶማሊ ክልል ዳዋ ዞን በተከሰተ ድርቅ ሰበብ ከ60 ሺሕ በላይ አርብቶ አደሮች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 23 2014 ― በሶማሊ ክልል ዳዋ ዞን በተከሰተ ድርቅ ሰበብ ከ60 ሺሕ በላይ አርብቶ አደሮች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ መባሉን አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡

ድርቁ የተከሰተበት የሶማሊ ክልል ዳዋ ዞን በቅርቡ በተመሳሳይ በዝናብ እጥረት ምክንያት ድርቅ ካስተናገደው የኦሮሚያ ክልሉ ቦረና ዞን ጋር ተመሳሳይ የአየር ንብረት የሚጋራ መሆኑ ተገልጧል፡፡

በዚህ በዳዋ ዞን አስተዳደር ተመርቶ በተደረገው ጥናት 47 ሺሕ 215 እንስሳት መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል በርካታ ግመሎች እና የቤት እንስሳት እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

ከድርቁ ጋር በተገናኘ አስር ትምህርት ቤቶችም መዘጋታቸውንም ጥናቱ አመልክቷል፡፡

በክረምቱ ወራት በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት የጉጂ እና ቦረና ዞኖች 395 ሺሕ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ከዚህ ቀደም ተነግሯል፡፡

የጉጂ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ገመቹ እንደገለጹት፣ በዞኑ በሚገኙ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎች ባለፈው የምርት ጊዜ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት በቂ ምርት አላገኙም፡፡ በጉጂ በአሁኑ ወቅት በዞኑ ከሚገኙት 13 ወረዳዎች መካከል በስድስቱ ድርቅ ተከስቷል፡፡

ይህን ተከትሎም በዞኑ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 229 ሺሕ ያህል ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ከእነዚህ የምግብ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል ሴቶች እና ሕፃናት እንደሚገኙበት ነው የተገለጸው፡፡

በሌላ በኩል የቦረና ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኃላፊ አቶ ሊበን ከበደ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙት ሁሉም ዞኖች በሚባል መልኩ በድርቅ ተመተዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ከሆነ በአሁኑ ወቅት 166 ሺሕ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡  

በዞኖቹ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ የመንግስት እና የግል ተቋማት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው፣ ከችግሩ ስፋት አንጻር ድጋፉ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img