Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሕወሓት በሌሎች ኃይሎች የቴክኖሎጂ እና የመረጃ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኛል ሲሉ ጠ/ሚ ዐቢይ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 23 2014 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሚመሩት መንግስት ጋር ውጊያ ውስጥ የሚገኘው ሕወሓት፣ ‹‹እኛ ካለን የቴክኖሎጂ አቅም በላይ ያላቸው›› ባሏቸው ኃይሎች በቴክኖሎጂ እና በመረጃ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በትላንትናው እለት ከሚኒስትሮች እና ከሚኒስቴር ዴኤታዎች ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት የተመለከተ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አያይዘውም በወሎ ግንባር «የውጪ ዜጎች» ከሕወሓት ወግነው በጦርነቱ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳታዎቹ «የኢትዮጵያ ዝርያ የሌላቸው ነጮች እና ጥቁሮች›› መሆናቸውን ከመጥቀስ በዘለለ ማብራሪያ አልሰጡም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የመጣው የሕወሓት ኃይሎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት የአማራ ክልል ከተሞች የሆኑት ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን መያዛቸው መዘገቡን ተከትሎ ነው፡፡

በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተላለፈው በዚህ ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱን አሁንም መንግሥት እንደሚያሸንፍ ርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሕወሓትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ «ምንም ጦርነት ሳናደርግ ይህን ሃይል ብንቀበለው፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትናንትናውን ህወሓት ሳይሆን የዘመነውን ህሓሃት ለመሸከም ጫንቃዋ አይችልም» ብለዋል፡፡ አክለውም «አሁን ማሸነፍ መሸነፍ ሳይሆን እኩይ አላማው የሚሳካበት ጭላንጭል መንገድ የለም፣ የኢትዮጵያ አውድ ተቀይሯል። ከተቀየረው የኢትዮጵያ አውድ ጋር መቀየር የሚችል ኃይል አይደለም» ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አሁን እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት አላማ «በትጥቅ ኃይል መንግሥት የመፍጠር ፍላጎት ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው ማድረግ ነው» ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ሆነው የጠላት አፍ ሆነው ‹‹ሕዝባችንን ትጥቅ የሚያስፈቱ›› ያሏቸው አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ የተነገሩት ዐቢይ፣ በጉዳዩ ላይ ከክልሎች ጋር መነጋገራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹እዚህ ያላችሁም አስፈጽሙት›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹እንደዚህ የነጻ ሚዲያን በማስመሰል የሚጫወቱ አሉ፤ ነጻነት በአገር ቀልድ አይሰራም፤ ብዙ ድራማዎች አሉ፤ እርሱ ላይ ጠንከር ያለ ነገር ይወሰዳል» ሲሉም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img