አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 23፣ 2014 ― በአዲስ አበባ ከተማ የጦር መሳሪያ ያላቸው ግለሰቦች በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያስመዘግቡ የከተማው ሰላምና ደህንነት አስተዳደር ቢሮ አሳስቧል፡፡
ይህንኑ የከተማ አስተዳደሩ የሰላምና ደህንነት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
የጦር መሳሪያን በተመለከተ ሕጋዊም ሆነ ያላስመዘገቡ አካላት በሁለት ቀናት ማስመዝገብ አለባቸው ብለዋል።
የጦር መሳሪያው በመንግስት ከታወቀና ህጋዊ ከሆነ በራሱ የአካባቢውን ፀጥታ እንዲያስጠብቁ ይደረጋል ብለዋል። መሳሪያ ያላቸው አካላት አካባቢያቸውን መጠበቅ የማይችሉ ከሆነ ለቅርብ ሰው ወይም ለመንግሥት በአደራ ሰጥተው እንዲጠበቅበት ይደረጋል ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘውም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመንደር እርስ በርስ ተደራጅተው አካባቢውን እንዲጠብቁ ተፈቅዷል ማለታቸውን ተመላክቷል፡፡ አደረጃጀቱም ከፀጥታ ተቋማት ጋር እየተናበበ አካባቢውን መቆጣጠር እንዳለበትም ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፀጥታ ሰላም ቢሆንም፣ ውዥንብር የሚፈጥሩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው ያሉ ሲሆን፣ የፖሊስና የመከላከያ ፀጥታ አካላት ከኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሰላምና ደህንነት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባን ሰላም ለማስከበር የፍተሻ ስራዎች በየተለያዩ ቤቶችና ንግድ ቦታዎች ፍተሻ እንደሚደረግባቸው ጠቁመው፣ ለዚህም ህብርተሰቡ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል ነው የተባለው፡፡